የዛሬዉ ታሪካችን በቅጡ ካልተመዘገበ ነገ በተረት ተረት መልክ እንደሚወራ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ ታሪኩ ሙሉ ካልሆነ ፤ አንባቢን ማደናገር በማለት ከማለፍ ይልቅ ማወቅ የተቻለዉን ያህል በማለት ለሌሎች ባለተራዎች በመተዉ እነሱዉ እራሳቸዉ እንዲቆፍሩት ማድረግ የተሸለ ነዉ፡፡ የታሪኩን ጭብጥ ለመረዳት ነበር ቀጥር አንድ የገስጥ ተጫነን መፅሃፍ ማንብብ መልካም ነዉ፡፡
ደርግ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ/ም ከተራ ወታደር አስከ ሻለቃ በሚደርሱ መለዮ ለባሾች በ4ኛ ክፍለ ጦር ግቢ ሲመሰረት የአቢዮቱ አንዱ ገጽታዉ በማዕረጋቸዉ ከፍ ከፍ ያሉትን ያገለለበት ምክንያት ባለትልቅ ማዕረጎች ከንጉሳዊ ስርዓት የሚያገኙት ጥቅማጥቅም የተሻለ በመሆኑ የአቢዮቱን ሂደት በሙለ ልባቸዉ አይተባበሩም ወይም ያሰናክላሉ በማለት ነዉ፡፡
110 ገደማ የሚደርሱ አባላት ያሉት ደርግ ''ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!!!'' የሚል መፈክር አንግቦ ወሳኝ የሆኑ አገራዊ ዉሳኔ አሳልፎል፡፡ የመሬት ለአራሹን ጥያቄ በመርህ ደረጃ የመለሰበት በዋናነት የመጠቀስ የደርጉ እርምጃ ነዉ፡፡ ''ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም !!!'' መርህ ግን ብዙም ሊዘልቅ አልቻለም ፡፡ ደርግ 53 የሚደርሱ የንጉሱ ባለስልጣናትንና የእራሱን ሰዎች በጅምላ ገደለ፡፡
ደርግ የዝቅተኛ መኮንኖች ጥርቅም እንደመሆኑ እርስ በርስ ለመደማመጥ አልቻለም፡፡ ይልቁን ይህ የ110 ሰዎች ስብስብ የደርግን ጡንቻ ለመቆጣጠር የመጣበትን የጦር ክፍል ተንተርሶ አልያም ተቀናቃኙን ጠልፎ የሚጥልበትን ሴራ በመጎንጎን ሁሉም የእየራሱን ቡድን የበላይነት ለመቆጣጠር ሙከራ በሚያደርግበት ሰዓት ነዉ ከፊሉ ደርግ ከሁለቱ መቶ አለቆች ቡድን ጋር የተላተመዉ፡፡ ሁለቱ መቶ አለቆች በዉቀቱ ካሳ (የክቡር ዘበኛ ተወካይ) እና ስለሺ በየነ (የአየር ወለድ ተወካይ) የሃረር ጦር አካዳሚ ምሩቆች በመሆናቸዉ የደርግ መዘዉር ከሻለቃ መንግስቱ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ምሩቅ እንዲወጣና ወደ እነሱ ቡድን እንዲሄድ ይፈልጋሉ፡፡
ሁለቱ መቶ አለቆች የሻለቃ መንግስቱ ቡድን ተቀናቃኞቹን በፀረ-አቢዮት ሰበብ አንድ ሁለት እያለ ሲለቅማቸዉ ታዲያ ወደ ትዉልድ አካባቢያቸዉ ጎጃም ፤ማቻክል ወረዳ፤ ትሳስዳር ቀበሌ ለአንደኛዉ መቶ አለቃ የስጋ ዝምድና ካለዉ ፊዉዳል ዘንድ ሄደዉ መሸጉ፡፡ መቶ አለቆቹ የመሸጉት ምናልባት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ህይወት ለማቆየት ብለዉ እንጂ ከዳር ዳር በተዛመተዉ አቢዮት ፀረ-ደርግ አቋም ይዘዉ ከለላ እናገኛለን በሚል ቅዠት አይመስለኝም፡፡
በደርግ ስብስብ ቀስ በቀስ እየጎሉ የመጡት ሻለቃ መንግስቱ (ጠላቶቻቸዉን አድብተዉ እስቲያጠቁ ድረስ ጥርሳቸዉን ብልጭ እያደረጉ የማዘናጋት ልዩ ተሰጥኦ እንዳላቸዉ የነበር መፅሃፍ ደራሲ ይገልጾቸዎል፡፡) እነዚህ ሁለቱ መቶ አለቆች ሲሰወሩ የሚደመስሳቸዉ ሃይል ልኮ ነበር፡፡
ይህን አባቴ የተረከልኝን ታሪክ ነዉ ላዎጋችሁ የመረጥሁት፤ ደርግ የላከዉ ሃይል ጎጃም ያረፈዉ በማቻክል ወረዳ ፤ አማኑኤል ከተማ ፤ አማኑኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን ወታደር ለማዘመን ድርጎ እንዲኖረዉ ብዙ ጥረት ካደረጉ በኋላ በንጉስ አፄ ሃይለ ስላሴ ጊዜ ጀምሮ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ወታደር የተገነባ ቢሆንም በደርግ ሁለቱን መቶ አለቆችች እንዲደመስስ የተሰማራዉ ጦር ግን በትሳስዳርና አካባቢዉ ቀበሌ አርሶ አደር ሃብት ላይ ዘመተ፤ ከብቶቹን እየነዳ አማኑኤል ከተማ በሚገኘዉ ካምፑ ፈንጠዝያ አደረገ፡፡
ይህ ሃይል ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ነዉ ሁለቱን መቶ አለቆች በግዳይነት የጣለዉ፡፡ አስጠልለዎቸው የነበሩትን ፊዉዳል ግን ''የአቢዮቱ ተጠቃሚ'' ለነበረዉ የአርሶአደር የቤት ስራ ሰጥተዉ ተመለሱ፡፡ ፊዉዳሉ ብዙ አልቆዩም በአርሶአደር እጅ ከሸጥ ውስጥ ከተደበቁበት ተገደሉ፡፡ እነዚህ መቶ አለቆች ከክብር ዘበኛ እና አየር ወለድ የጦር ክፍሎች ተወክለዉ ሲሄዱ የኢትዮጵያ አቢዮት የለዉጥ አካል ሊሆኑ ነበር፤ አቢዮት ልጆቾን ትበላለች እንደሚባለዉ ከአያሌ የአቢዮቱ ሰለባዎች ሁለቱ ሆኑ፡፡ እነዚህ መቶ አለቆች በተገደሉበት አካባቢ የተቀበሩ ሲሆን ዛሬ ድረስ ገብስማ ቀበሌ ዉስጥ የደርጎች መቃብር የሚባል ቦታ አለ፡፡