“ህገ መንግስቱ የተጻፈበትን ወረቀት ያህል ዋጋ አያወጣም፡፡’’ ይህን ንግግር በ1997 ዓ/ም በተደረገው በምርጫ ዋዜማ በተደረገ የምርጫ ክርክር ላይ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርየም የተናገሩት ነው፡፡ ፕሮፊሰሩ አክለውም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህገ-መንግስት ሳይሆን ህገ-አራዊት ነው፡፡ መሬት ላይ እየተገዛን ያለው በህገ-መንግስት ሳይሆን አዉቀቱም ሆነ ክህሎቱ የሌላቸው የወያኔ ባለስልጣናት ህግን ተክተው በእውር ድምብራቸው በሚያስተላልፉት መመሪያ ነው፡፡
እውን ወያኔ ለኢትዮጵያን የህገ-መንግስት ታሪክ እንዳስረከባት ፤ ከእርሱ ዘመን እንደተጀመረ አድረጎ የሚተርከው ወያኔ ይዞልን የመጣውን ህገ መንግስት እራሱ ያከብረዋል?
ወያኔ የምርጫ 1997 ዓ/ም ምርጫ ከፈጠረበት ድንጋጤ ማግስት ከህገ-መንግስቱ ጋር ተጻራሪ የሆኑ በርካታ ህገጎችን አውጥቶል፡፡ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ማሽን ቀን ከሌት ሀገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ እያለ ተቃዋሚዎችን የሚከስ ቢሆንም በተግባር ግን ህገ-መንግስቱን ወይንም ህገ-መንግስትን ማላገጫ ያረገ ቡድን ቢኖር ወያኔ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ከጫካ ይዞት በመጣው እውቀት 22 ዓመት የመራትን አገር የዩንቨርስቲን በር በትምህርት ከዚያም በመምህርነት የረገጡት ሃይለማርያም ደሳለኝ አገር መምራት አይችሉም ተብለው ወይም ሌላ ድብቅ አላማ ተረግዞ ህገ-መንግስት ተጥሶ (አንቀፅ 75) ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ታኮ ተጨመረለት፡ድንቄም የማዕዘን ድንጋይ፤ አልሰማህም ይላል የአራዳ ልጅ አመንኪዮ አልባ ወይንም ሁለት መለኪያ ለአንድ ጉዳይ ሲያጋጥመው (double standard)፡፡
በቅርጽ ብቻ ፓርላመንታዊ ስርዓት የዴሞክረሲያዊ መንግስት መገለጫ ቢሆን ወያኔ የሚመራት ኢትዮጵያ ከአለም ቁንጮ ዲሞከራት አገር መባል በቻለች፡ የህግ ቋሚ ኮሚቴ፡ የማህበራዊ ቋሚ ኮመቴ እየተባለ ፐሮፊሽናል ፓርላማ ለማስመሰል የማስመሰያ ስም ይሸከማል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን በዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ፍልስፍና የሃሳቦች መንሸራሸሪያ መድረክ ሳይሆን የወያኔ ከበሮ ብቻ የሚደለቅበት የተዋረደ ቦታ ሁኖል፡፡
በአንጻሩ በንጉሱ ጊዜ የስልጣን ምንጭ ህዝቡ ሳይሆን መለኮታዊ ስልጣን በሆነበት ወቅት፤ ርዕስታቸውን ጋሻ አድርገው ወደ ምክር ቤት የመጡ የፓርላማ ተወካዮች በአንጻራዊ መንገደድ የመጡበትን አካባቢአዊ ቸግሮቻቸውንና ፍላጎታቸውን ለንጉሱ ምክርቤት ያለምንም መሸማቀቅ ያቀርቡ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ዛሬ ዛሬ ወያኔወች በህገ መንግስቱ ውስጥ ያሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የረሱዓቸው ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንኳን የወያኔን ደጅ መጥናት ግድ ብሏል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ሰለሚያስተጓጉል የተከለከለ ነው፡፡ እንግዲህ ወይ ህገ-መንግስታዊ ማሸሻያ ያድርግ ወይስ ደግሞ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚል አሰልች የሆነ የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ይቁም፡፡
ከሶስት ሳምን ወዲህ በጊንጭ ተነስቶ በመላው ኦሮሚያ እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ አመጽ የመብት ጥያቄ ነው፤ ይህ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ግን ከአምባገነኑ ወያኔ ያገኘው የሃይል ምላሽ ሲሆን የብዙ ሰዎችን ሂዎት ቀጥፎል፡፡ ህዝብ ተማሪ፤ አርሶ አደር፤ ቀን ሰራተኛ፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ ፤ ሲቪል ሰርቫንት፤ ከልጅ እስከ አዎቂ የተሳተፈበት ሰላማዊ የህዝብ ጥያቄ ጸረ-ሰላም ሃይሎች ከሆላ ሁነው የሚቀሰቀሱት የሽብረ ሴራ ማለት ወያኔ የመከበብ ስሜት ውስጥ ያለ ፈሪ እና ጠባብ ቡድን መሆኑን ያመለክታል፡፡
የዴሞክራሰ ስርኣት መገለጫ የሆኑት ሶስቱ አውዶች ህግ አውጭ፤ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈጻሚ ፤ አንዱ በአንዱ ጣልቃ ገብነትን አቁመው ነገር ግን ህጋዊ በሆነ መንገድ አንዱ አንዱን የሚቀቋጣጠርበትን መንገድ የተበጀ ሲሆን አገር ነጻ ህዝቦቾም እራሳቸውን መቻል ይችላሉ፤ ነጻነት ካለ ኮብልስቶን ዳቦ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ የፀጥታ ሃይለም ህዝብን ሳይሆን ዳር ድንበር (ወሰንን) መጠበቅ ይሆናል ተቀዳሚ ስራው፡፡
ዛሬ ወያኔ ከጎንደር እስከ ጋመምቤላ ያለውን ለም መሬት ለመስጠት እንደተዘጋጀ ይታወቃል፡፡ መለስ ዜናዊ ሞት ሳይቀድማቸው ለሚወዳቸውና ለሚወዱት ፓርላማ አባላት ሱዳን ከኢትዮጵያ አንዳችም መሬት አትፈልግም ነገር ግን የኢትዮጵያ አርሶአደር በወረራ ያዘውን መሬት ግን ለመመለስ ዝግጁ ነን ብለው ነበር፡፡ የወያኔ የስልጣን ጥም ለማርካት በህዝብ ድምጽ መተማመን ስለማይችን በጎረቤት አገራት ላይ መንጠላጠልን መርጦል፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይሉሻል ይሄ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ያለው ህዝባዊ ቁጣ የተጠራቀመ የህዝብ ብሶት ነጸብራቅ ሲሆን ፤ የኦሮሚያ አርሶአደርና ተማሪ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ጉሊት ሻጭ እናት ፤ በየከተሞች ስራፍለጋ የሚባዝነው የደቡብ ወጣት፤ በስሙ የሚነገድበት ነገር ግን ተጋዳላይ ጎረቤቶቹ ጮማ ሲቆርጡ የሚያዛጋው ትግሬ ፤ እንደ አበደ ውሻ እየታደነ ያለው አማራ ፤ በጋምቤላ በቤሻንጉል በኦሞ እና በአፋር የሚፈናቀለው አርብቶ አደር ብሶት ጭምር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ወጣት ዥንጉርጉር የሆነውን ባህልህን፡ የሃማኖትና የቋንቋ ልዩነትህን እንደ ጌጥ ወስደህ ለዘረኞችና ለከፋፋዮች ሴራ ሳትንበረከክ ፤ የኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋ በእኛው አጅ መሆኖነ ተገንዝበህ በህዘባዊ ፤ ሰላማዊ ትግል የስልጣን ባለቤትነታችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡
አንድነት ሃይል ነው፤ ወራሪዎችን የመከተ ህዝብ ለባንዳዎች አያንስም፡፡ ኢትዮጵያን እ/ር ይጠብቃት፡፡ አብራሃም ለቤዛ