Followers

Friday, August 11, 2017

ግብር ለምን ዓላማ?



በኢትዮጵያችን ገቢ ለልማት ከቴሌቪዢን ፕሮግራም ባለፈ በኢትዮጵያ ለልማት ይውላል ወይ ነው ቁልፋ ጥያቄ፡፡ በብድር ፤ በእርዳታ ፤ ኢትዮጵያዊያን ለቤተሰቧቻቸው ከስደት አገር የሚልኩት ገንዘብ እንዲሁም መንግስት የሚሰበስበው ግብር (የአገር ውስጥ ገቢ) የገቢ ምንጮች ናቸው፡፡ ገቢ ለልማት ብንልም ቅሉ ገቢው ልማት ላይ መዋል አለመዋሉን መቋጣጠር የሚችል የማህበረሰብ ተሳትፎ መፍጠር አልቻልንም፡፡ እኔ አውቅልሀለሁ የሚል ገዢ ፓርቲ ያልሁህን አምጣ የማለት የሞራልም የህግም መብት የለውም፡፡ አሳታፊ እና ተጠያቂነት ባለበት ስርዓት ግን ዜጓች ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታቸው ነው፡፡ የሚወዶትን አገራቸው ማልማት፡፡ ቃልና ተግባር ለየቅል ሆነ እንጂ፡፡ ግብር አስፈፃሚው አካል ሙሠኛ ከሆነ እንዴት ግብር ከፋዩ ሀገርህን ስለምትወድ ብለን እናሳምነው? የተጣለብኝ ግብ ፍትሀዊ አይደለም ሲል የይግባኝ ስርዓት ከሌለን ወይንም ሁሉንም ነጋዴ በእኩል አይን የምናይበት ፍትሀዊ አሰራር ግብር ሰብሳቢው አካል ላይ ከሌለ እንዴት ግብር መሠብሠብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ የግብር ተደራሽነት ከሌሎች አፍሪካ አገሮች አንፃር ሰፊ መሠረት እንደሌለው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ነው በየአመቱ የሚታወጀው በጀት 50% በላይ በብድርና ዕርዳታ ይሸፈናል እየተባለ ቃል የሚገባው፡፡ ነገር ግን በዕርዳታ የሚመጣውም ገንዘብ ሆነ ብዙ ዳፋ ለትውልድ እያስተላለፍንለት ያለው ብድር በሙስና ይባክናል፡፡ የኦዲት ባለሙያዎች ምስጋና ይግባቸውና በሪፖርታቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየገለፁት ነው፡፡ የግብር መሠረት ለማስፋት አሳታፊና ፍትሀዊ ስርዓት ያስፈልገናል፡፡ በግብር የተማረረው ዜጋም እንደዚህ ነው ብሷቱን በስነ-ቃል እየገለፀ የመጣነው፡፡
******ዓፄ ቴዎድሮስ ጎጃ ዘምተው ሕዝቡን በዘረፉበት ጊዜ ጉዳት የደረሰባት አንዲት ሴት እንዲህ ብላ አለቀሰች፡፡
ልብሴንም ገፈፈው፤ ለበሰው እርዘኛ፤
በሬየንም ነዳው አረደው ነፍጠኛ፤
እህሌን ዘረፈው በላው ቀለብተኛ፤
ንጉሥ የቀረዎ ጥቂት አማርኛ፣
 ምነው ሆድ አይዘርፉ አርፌ እንድተኛ፡፡

*****
ራስ ኃይሉ በዘመኑ የጎጃምን ሕዝብ (የኔ ቢጤ ደሀን ለማኙን ሳይቀር) “ግብር ክፈልእያለ በአስጨነቀበት ወቅት ሕዝቡ እንዲህ ብሎ ስሜቱን ገለጠ፡፡
ጎመኑን ቀርድጄ ጥሬውን በላሁት፣
 እንዳላበስለውም የጭሱን ፈራሁት፡፡
ራስ ኃይሉ ጭስ የሚጨስባትን እያንዳንዷን ጎጆ እያስቆጠሩ፣ ግብር ያስከፍሉ ስለነበር በጎጃም ሚስት ያገቡ ወጣቶች ጎጆ አይወጡም ነበር፤ ትልቁ ቤት እየተዘረጠጠ በታዛ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አባቶቻችን ይናገራሉ፡፡
አሁንስ እንዲህ ብለን ብንቃኝ አይቻል ይሆን?

ገቢ ለልማት መሆኑን አውቃለሁ፤
ኢትዮጵያ አገሬንም በጣም እወዳለሁ፤
የቄሳርን ለቄሳር ቅዱስ ቃሉ ይላል፤
ኮረጆ ገልብጠህ ድምጤ የሰረቅከኝ በብር ማን ያምንካል፡፡ 

No comments:

Post a Comment