Followers

Tuesday, April 19, 2016

የምርጫ ፖለቲካ ወይስ ህዝባዊ እምቢተኛነት?



የይስሙላ ምርጫ
የምርጫ ፖለቲካ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ይህም ሲባል ግን ከምርጫ ቀን በፊት አስቀድመው የሚሰሩት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች አንጻራዊ እና እየተሸሻለ በሚሄድ አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓት ፣ የፖለቲካ መድረክ ክፍት ሁኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት መደራጀት ሲችሉ እና ገለልተኛ ምርጫ አሰፈጻሚ አካላት ሲኖሩ እና ሂደቱን የሚዳኝ ነጻ የፍትህ ስርዓት ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ባልተሞሉበት ሁኔታ ወደ ምርጫ ሂደት ለምን እንደሚገቡ ሲጠየቁ  እነዚህ ጉዳዮች ቢሞሉ ቀድሞዉኑ ወደ ፖለቲካ ትግል እንደማይገቡ ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ትግል ከዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ ባለፈ የፖሊሲ አማራጮችን ይዟ ወደ ትግል የሚገባበት ጭምር ነው፡፡
ወያኔ/ኢህአዴግ የይስሙላ ምርጫዎችን ሲያካሄድ ከቆየ በኋላ በ1997 ዓ.ም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስመሰያ እና እርዳታ ማግኛ በሚል ሰበብ እውነተኛ የምርጫ አየር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ነፈሰ፡፡ ሆኖም ድሮም ወያኔ በመርህ ደረጃ ሳይሆን በውጫዊ ግፊት ያደረገው ስለነበር ለኢትዮጵና ህዝቧ ብሩህ መፃኢ-እድል እና ለመድብለ ፓርቲ ምስረታ መሰረት ሊሆን የሚችለውን አጋጣሚ አጨልሞታል፡፡
ታማኝ ተቃዎሚ በሚል ፈሊጥ  ለወያኔ አጎብደጅ ፣በወያኔ መመሪያ ሚሰራ፣ በወያኔ የምርጫ ስነ ምግባረ የሚገዛ እየተኮለኮለ በህጋዊነት ስም ምርጫ ቀን ሲመጣ ድርጎ ይሰፈርላቸዎል፡፡ ገዢው ቡድን ለምርጫ ፉክክር ለፓርቲዎች የገንዘብ ድጎማ እንደሚያደርግ ፣ ይህም ከአለም የተለየ ተራማጅ መንግስት እንደሚያደርገው ይመጻደቃል በአንፃሩ ግን ፓርቲዎች ድጋፍ የሚያደርጉለቸውን ግለሰቦች እንዲያሳዉቁ የሚል አዎጅ አውጥቶ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአገራችን እንዳያንሰራራ የተቻለውን ያደርጋል፡፡
ፓርቲወችን ለማፍረስ ቀን ከሌት የሚኳትን ፣ በፓርቲዎች ውስጥ ሰላዮቹን አስርጎ የሚያስገባ እንዲሁም የፓርቲዎችን ቢሮ በጠራራ ፀሃይ ሰብሮ የሚገባ ቡድን ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች ታማኝ የሆነ እና ታማኝ ያልሆነ ተቃዎሚ እያለ ደረጃ ለመመደብ የሞራል የበላይነት የለውም፡፡  ነገር ግን በሸፍጥ የፖለቲካ ባህል ላደገ ቡድን እንደ ፖለቲካ ስልት ሊቆጠር ይችላል፡፡
ፖለቲካ ለህዝብ ስልጣን የሚደረግ እስከሆነ ድረስ ከእውነት ጋር ተፃራሪ አቋም ሊኖረረው አይገባም፡፡ ለህዝብ እና በህዝብ የሚደረግ የፖለቲካ ትግል እስከሆነ ድረስ፡፡
ጩኸቴን ቀማኝ
ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል እንደሚባለው፤ ገዢው ቡድን እራሱን የተዋሃዱትን የፖለቲካ ችገሮች በሙሉ በሌሎች ተቀናቃኞች ላይ ማላከክ እንደ ፖለቲካ ስልት ችክ ብሎ ይጠቀምበታል፡፡ ለዚህ ሃሳብ ትክክለኛ እና ተጨባጭ ማስረጃ ሁኖ የሚቀርበው በ1997 ዓ.ም ምርጫ ፉክክር ያሸነፈው ቅንጅት አመራር ተካሳሾች ላይ ገዢው ቡድን በመጀመሪያ ያቀረበው ትንሽ ቆይቶ ያነሳው የዘር ማጥፋት ክስ ነው፡፡ ገዢው ቡድን እራሱ አንድን ዘር፤ አማራ የተባለውን የሕበረሰብ ክፍል በመለየት በትግል ማኒፊስቶው ዋነኛ ጠላቱ አድርጎ ለስልጣን ኮርቻ ለመድረስ በቅቶል፡፡ ከተራበ ህዝብ በሚሰበሰብ መዎጮ በሚተዳደር የፕሮፓጋንዳ ማሽኖች ቀን ከሌት የስልጣን ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን የትምክህተኝነትና የጠባብነት ችግር አለባችሁ፤ውስጣችሁን ከአሻባሪ ድርጅቶች ማጽዳት አለባችሁ የሚለው ማስፈራሪያ ፓርቲዎችን የፕሮፓጋንዳ ሰለባ በማድረግ ጊዜያቸውን ተጠቅመው የአደረጃጀት ስራቸውን ሰርተው ጠንክረው እንዳይወጡ ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የምርጫ ፖለቲካ ለመድረግ ካለው ህልም ነው፡፡  ከፕሮፓጋንዳ ባለፈም የፓርቲዎችን በጠንካራ ታጋዮች ላይ ውክቢያ ፣ ግድያ እና እስር አየፈጸመ ይገኛል፡፡ ይባስ ብሎ ገዢው ቡድን የሚገድላቸውን የፓርቲ አባላት የፖለቲካ ሰውነት ጭምር ለመካድ ተራ የፕሮፓጋንዳ ስራ  ይሰማራል፡፡ ወጣት ሳሙኤል አወቀ  የደብረ ማርቆስ ሰማያዊ ፓርቲ አመራርን ፤ የኦፌኮን የሰላሌ ወጣት አመራር ማስታዎስ በቂ ነው፡፡
አባይ አባይ የወያኔ ሲሳይ!
አባይ አባይ የአገር ሲሳይ የሚለው ስንኝ አባይ ለታችኛዉ ተፋስስ አገሮች ፣ ለሱዳንን ግብፅ ያለውን ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ለማመልከት ነው ነገር ወያኔ/ኢህአዴግ ለራሱ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ አባይ ረጅም ወንዝ አንደመሆኑ ይመስል  ከአባይ ግድብ (ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ) ጋር በተገናኘ ረጃጅም ወሬ ነው ነው የሚጠረቀው፤ ማስታወቂያዉ ፤ፕሮፓጋንዳው ሁላ ረጅም ነው፡፡  የአባይ ግድብ ከሃይል ማመንጫነት ባለፈ ድህነትን ተረት ተረት ለማድረግ እንደሚረዳው ይገልፃል ፤ ስያሜውንም የኢትዮጵያ ህዳሴ በማለት ያንቆለጳጵሰዎል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ መሰራቱ ልዩ ያደርገዎል ይባላል፡፡ ለኢትዮጵያዊያን ማን እንዲሰራላቸው ነው የተፈለገው ? በአንፃሩ ኑሮ ከአቅሙ በላይ የከበደው እና የመንግስት ጭቆና ያስመረረው ኢትዮጵያዊ አባይ ግንድ ይዞ መዞረን አቁሙ ደመዎዛችንን ይዞ ይዞራል ፤ አባይ ከመገደቡ በፊት ጭቆና ይገደብ እያለ ምሬቱን ይገልፃል፡፡ የአባይን ግድብ ለፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ከማለም የተነሳ የአባይ ግድም የመሰርት ድንጋይ ሲጣል በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው ወደ ጎን ተደርጎ  ከጉሮሮ እየተነጠቀ ቦንድ እንዲገዛ ለሚገደደው  ህዝብ የአባይ ግድብ አምስተኛ አመት ክብረ በዓል የሚል ሌላ ማወናበጃ ይነገረዎል፡፡  የአባይ ግድብ 50 % (ግማሽ በመቶ) ተጠናቆል እየተባለ መረጃ እየተሰጠ ባለበት ሰዓት ለኢትዮጵያ ህዝብ  በአምስት ያልተጠናቀቀበት ምክንያት ለምንድን ነው የማይነገረው ? እስከመቼ ሊቆይ እንደመቺልስ የማይነገርበት ምክንያት ምናልባት  እኛው እንደጀመርነው እኛዉ እንጨርሰው ፤ ተጨማሪ የስልጣን እድሜ ስጡን ለማለት ይመስላል፡፡ አባይ መገደብ ያለበት እንደ አንድ የዉሃ ሃብት የልማት እቅድ እንጂ ከሳሊኒ ኩባንያ ጀምሮ ግልፅነጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ መሆን የለበትም፡፡ መቼ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ የኔ ልማታዊ መንግስት ፈቅጅልሃለሁና ሳታሳውቀኝ እንዳሻህ አድርግ ያለው? ተጠያቂነት በሌለበት ስርዓት ውስጥ የህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በመሪዎች ደመ ነፍስ ነው አገር የምትመራዉ፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ዕድገት በተጠና መንገደ ለተከታታይ ሰምንት አመታት ባለሁለት አሃዝ እድገት እንደተመዘገበ  ከሚኒስተር ጀምሮ እሰከ ቀበሌ ካድሬ ድረስ ይደሰኮራል፡፡  ወያኔ ልማትን በፐሮፓጋንዳ አመጣለሁ ብሎ ካሰበ  ለኢትዮጵያ ህዝብ በነፍስ ወክፍ ራዲዮን ቢያከፋፍል ይሻለዎል፡፡ የመረጃ ምንጮችን ለማፈን የሚደክመውን ያህል የራሱን ውሸት ለማሰራጨትስ ምናለ ሬድዮ ቢያድለን፡፡  በሴፈቲሬዲዮ ፕሮግራም ቢያቅፍ፡፡
ልማታዊ መንግስት
የልማታዊ መንግስት ፅንሰ ሃሳብ መንግስት ሰፊዉን የኢኮኖሚ ድርሻ ይዞ ትላልቅ ልማቶችን የሚያካሂድበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲሆን ከደቡብ ምስራቅ ኤሺያ አጋረት (The Tigers) ባሻገር የአውሮፓ አገራትን፣ አሜሪካን ጨምሮ በዚህ መንግድ እንዳለፉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ በእኔ እይታ ወያኔ/ኢህአዴግ አንድም የልማታዊ ቅንጣት ታህል እርሾ የለውም፡፡ ከፋፋይ እና ዘረኛ የሆነ ቡድን ልማታዊ መንግስት ነኝ ቢል ከዳር ዳር ያለውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማሰለፍ ስለማይችል ሁሉን አቀፍ የሆነ ልማታዊ  እና በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላይ ሊታይ የሚችል የኢኮኖሚ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ነገር ግን እራሱን ልማታዊ ብሎ መጥራት መልከጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለዉ አገርኛ አባባል እንደ ፖለቲካ ስልት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡
ህዝባዊ እምቢተኝነት
ይህ ስርዓት  ሰላማዊ የትግል በሮችን በመዝጋት ፤ ሰላማዊ ታጋዮችን በአምሳያዉ ባዎቀረው የፍትህ ስርኣት እየታገዘ በማሰቃያ እስር ቤቶቹ እያጎረ ይገኛል፡፡ ስርዓቱ አስመሳይ እንደመሆኑ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሚመረቅበት ሰዓት መለስ ዜናዊ መንግስታቸዉ ለአፍሪካዊያን መሰባሰቢያ በቀድሞ ኢትዮጵያ ስርኣት (ደርግ) የማሰቃየ ቦታ የነበረዉ ዓለም በቃኝ እስር ቤት ለአፍሪካዊያን መለገሳቸውን በኩራት ተናግረዉ ነበር፡፡ ንግግራቸዉ አንድም የኢትዮጵያዊያን የስቃይ ታሪክ ማክተሙን ለግለፅ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ጠባቡ ገዢ መደብ ቡድን የፖለቲካ ተቀናቀኞቹን በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ጭካኔ በተሞላበት ፤ኢሰባዊ በሆነ መንገድ እያስተናገደ ይገኛል፡፡  ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ እና ወጣት ተስፋየ ተካልኝ የደረሰባቸውን የስቃይ ድርጊት ሳዳምጥ ትልቅ እልህ እና ቁጭት ነው የተጋባኝ፡፡ የሃሳብ ልዩነት ብቻ ላነገበ ኢትዮጵያዊያን ይህ ነው ወይ ምላሹ
ይህ ስርዓት የምርጫ ስርዓትን እየጠበቀ 99.6 አሸንፌአለሁ እያለ ከበሮ እያስደለቀ በስልጣን ላይ ለመቆየት ዓልሞ የተነሳ ሃይል እንጂ በአፍሪካ በህዝብ ብዛቶ ሁለተኛ የሆነች አገር ፤ ብዙሃን በሆነ የፖለቲካ ችግር ተወጥራ የምትገኝ አገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርንም ሆነ እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲገነባ አይፈልግም፡፡
በአንጻሩ ከየአቅጣቸው የሚነሱትን ህዝባዊ ተቃዉሞች ለመደፍጠጥ ከፍተኛ የሆነ በጀት እየመደበ የፀጥታ ሃይሉን ከመችው በላይ ጨካኝ እያደረገ ይገኛል፡፡ አምባገነኖች የትኛውንም ሃይላቸውን ቢገነቡም የሆላ ሞታቸውን  አስከፊ ሁኔታ እንደሚሞቱ ቢታዎቅመም ኢትዮጵያዊያን የተሸከሙት የጭቆና ቀንበር አሽቀንጥረዉ በመጣል አሁን አገራችን ካለችበት ሁናቴ ብሶ ለእዝበባዊ ትግልም ያለው እድል ጨርሶ ከመምከኑ በፊት በህዝባዊ እንቢተኛነት ጠባቡን ገዢ መደብ ማስወረድ ያስፈልጋል፡፡
ወያኔ/ኢህአዴግ እራሱን እንደብቸኛ የኢትዮጵያ አዳኝ የሚሰብከውን ደጋግመን ስንገመግም ኢትዮጵያን ለመበታተን ያለውን ስውር ደባ መረዳት አያዳግትም፡፡ ይች አገር ልተት ፈርስ ነበር፣ ከመፍረስ ያዳናት ወያኔ/ኢህአዴግ ነው የሚለው ፕሮፓጋንዳ አሰልቺ ነው፡፡ ለማጠናከርም 17 የሚደርሱ ነጻ አዉጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በሽግግር ዋዜማ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይታከልበታል፡፡ በአንጻሩ በአሁኑ ሰዓት የገዢው ቡድን አስኳል የሆነው ሕወሓትን ጨምሮ የነፃ አውጭነት ስማቸውን እንደያዙ የሚንቀሳቀሱ ከ50 የሚበልጡ በዘር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች ይንቀሳቀሳሉ፡፡
አምባገነኖችን ምርጫ በማይሉት ቦልት እያጀቡ ከመጓዝ ለኢትዮጵያዊያን ህዝባዊ እንቢተኝነት ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ህዝባዊ እንቢተኝነት ከዳር ዳር በማቀጣጠል ፤ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያቀፈ መሆን እንደሚችል በኦሮሚያ ፣ በአማራ እና በደበቡብ ኢትዮጵያ የሚታዩ እንቅስቃሴዎች ሁነኛ ምልክቶች ናቸው፡፡
ገዢው ቡድን በአፈናው እንደሚቀጥል ግልጽ ሲሆን የጸጥታ ሃይሉንም በስፋት ያሰማራል፡፡ ማንኛውም ትግል መሰዎትነት የሚጠይቅ ስለሆነ በዚህ ሂደት የሚመጣ መስዎትነት ቢኖርም ከኋላ ያለው ደጀን ህዝብ ትግሉን ያቀጣጥለዎል፡፡  ህዝባዊ እንቢተኝነቱ እየገፋ ሲሄድ የጸጥታ ሃይሉም ከኢትዮጵያዊያን አብራክ የወጣ በመሆኑ  የአቋም ለዉጥ ስለሚያደርግ ህዝባዊ እንቢተኝነቱ ተጨማሪ ሃይል እያገኘ ስለሚሄድ የህዝብ ነጻነት ቅርብ ትሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ተማሪው፣ ወጣቱ ፣ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ያለው ማህበረሰብ የቋንቋ እና የዘር ልዩነት ሳያደርግ በአንድ ላይ መሰለፍ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለ25 ዓመታት የተጎዝንበትን የክፍፍል መንገድ በማቋም በአንድነት መጎዝ ስንችል ብቻ ለኢትዮጵያ እውነተኛውን ህዳሴ እናበስራለን፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ! መፅናነትን ለጋምቤላ ኢትዮጵያወያን እመኛለሁ፡፡
አብራሃም ለቤዛ

No comments:

Post a Comment