Followers

Wednesday, September 11, 2024

የኢትዮጵያ ወራት እና ስያሜያቸው…!!!(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የኢትዮጵያ ወራት እና ስያሜያቸው…!!!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

 

በኢትዮጵያ የወራት ስሞች ከጥንት ጀምሮ የነበሩ፤ እርስ በርስ የተወራረሱ ናቸው። አማርኛ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተስፋፋ የመጣ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠን፤ ቃላቶችን ከግዕዝ፣ ከኦሮምኛ፣ ከአፋር፣ ከአረብኛ፣ ከጣልያንኛ እና ካመቸው ወይም ህዝብ የተቀበለውን የራሱ እያደረገ እና እያደገ የመጣ ቋንቋ ነው። ከመስከረም እስከ ጳጉሜ ያሉትን የወራት ስያሜዎች ከመረመርን ደግሞ፤ የዚህን እውነት እንረዳለን…!
ወደ ኢትዮጵያ የወራት ስያሜዎች እና አመጣጣቸው ከመሄዳችን በፊት ግን፤ በአገራችን ካሉት ቋንቋዎች መካከል በኦሮምኛም፤ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የወራት ስሞች በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ ስያሜ እንደነበራቸው ማስታወስ እንወዳለን። እነዚህን ልዩ ልዩ ስያሜዎች ወደ አንድ መደበኛ ቃል ማምጣት በማስፈለጉ፤ በኦሮምኛ በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን የወራት ስያሜዎች አንድ ላይ ሰብሰብ በማድረግ፤ የተሻለውንና በብዙዎች ዘንድ ጥቅም ላይ የዋለውን ቃል በመምረጥ፤ አሁን በመደበኛ የኦሮምኛ ቃል ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።
ለምሳሌ – የመስከረም ወር “ፉልባና” ይባላል። ስያሜውን ያገኘው ከሜጫ ኦሮሞ ነው። የጥቅምት ወር አንኮሌሳ ይባላል – ከአርሲ እና የባሌ ኦሮሞ የተወሰደ ነው። ህዳር ሶስተኛ ወር ሲሆን አርሲ እና ባሌ ሰደሳ ወይም ሶስተኛ ይሉታል። ቃሉም ከዚያ የመጣ ነው። የታህሳስ ወር በቱለማ ኦሮሞዎች ዘንድ ሙዴ ይባላል። የጥር ወር አማጄ ማለት ሲሆን ስያሜውን ከአርሲ እና ከባሌ ኦሮሞ ነው ያገኘው። ጉራንላ ከቦረና ኦሮሞ የተወሰደ ሲሆን፤ የካቲት ወር ማለት ነው። መጋቢት ወር ቢቶሴሳ ይባላል፤ ስያሜውን ከአርሲና ባሌ ነው ያገኘው። የሚያዝያ ወር ኤልባ የሚባል ሲሆን፤ ከቱለማ ኦሮሞ የተወሰደ ቃል ነው። ከግንቦት ወር ጀምሮ ያሉት ወራት፤ በአርሲ በባሌ፣ በቦረና፣ በጉጂ በቱለማ ተመሳሳይ ትርጉም ስላላቸው ያለምንም ምርጫ ግንቦት – ጫምሳ፤ ሰኔ – ዋጣባጂ፤ ሃምሌ – አዶሌሳ፤ የነሃሴ ወር ደግሞ ሃጋያ ይባላል።
ይህን ያህል የኦሮምኛን ወራት የቃል አመጣጥ ካወቅን ይበቃናል። ነገር ግን እዚህ ላይ የብሄሮችን ቋንቋ ተወራራሽነት ለማሳየት እንድንችል፤ በሲዳማ እና በኦሮምኛ ውስጥ የሚገኙ ወራት መኖራቸውን እናስታውሳቹህ። ለምሳሌ ሳደሳ፣ አርፋሳ፣ አንኮሌሳ፣ አዶሌሳ… የመሳሰሉት የወራት ስሞች በሲዳማ እና በኦሮምኛ ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ኩሼቲክ ወደ ሴማዊ ኢትዮጵያ በመሄድ፤ የአማርኛ ወራት ስያሜ ታሪካዊ አመጣጣቸውን ወይም ስለ ስነ-ውልደታቸው እንጨዋወታለን።
መስከረም – የመስከረም ወር አበቦች በየመስኩ የሚፈነዱበት፤ አደይ አበባ ምድሪቱን የሚያለብስበት ወር ነው። ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጪ፤ እጅግ ውብ የሆነ አገር ሲባል የሚሰሙት፤ ስለ ሮም እና ሮማውያን ነው። እናም ይህን በአበባ ያጌጠ መስክ – መስከ-ሮም ብለው ይጠሩታል። ይህን ለማረጋገጥ በተመሳሳይ መልኩ ረዥም እድሜ ያለውን የጉራጌ ሴማዊ ቋንቋ ማየቱ ይበቃል። በአብዛኛው የጉራጊኛ ቋንቋ መስከረምን…. መስከሮም ወይም መስከሮብ ይሉታል። አማርኛው ታዲያ ቃሉን ከርክሞ እና አስተካክሎ – መስከረም ብሎ ሰይሞታል።
ጥቅምት – በተለይ በገበሬው ዘንድ የጥቅምት ወር የሚታወቀው፤ ጥራጥሬ ተዘርቶ እሸት የሚያፈራበት ወር በመሆኑ ነው። ይህ ወር ከሌላው ወር በበለጠ፤ ለገበሬው እና ለከብቶቹ ጠቃሚ ወር ነው። በመሆኑም ጥቅም የሚሰጥ ጠቃሚት ወይም ጥቅምት ተብሎ የተጠራው በዚህ ምክንያት ነው።
ህዳር – ከመስከረም እና ከጥቅምት ወር በኋላ የሚመጣ ወር ነው። አንዳንዶች ህዳርን “ሃዳር” ከሚለው የግዕዝ ቃል ጋር በማዛመድ፤ “ከማደር” ጋር በማያያዝ – ታሪካዊ አመጣጡ ግዕዝ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ይጥራሉ። ሆኖም… የዚህ 3ኛ ወር ስያሜ የመጣው ባህር ተሻግሮ መሆኑ እውነት ነው። የህዳር ወርን… በግብጽ እና አረብ አገሮች፤ አቶር እና ሃቶር ሲሉት በእብራይጥ ደግሞ፤ አዳር በሚል ስያሜ ይታወቃል። በነገራቹህ ላይ ህዳር በግዕዝ ሲጻፍ ‘ኅ’ዳር ሲሆን፤ በትግርኛ ‘ሕዳር ነው። አማርኛው እንዳመቸው አድርጎ ሃሌታው ‘ሀ’ በመጠቀም ህዳር ይለዋል። የሆኖ ሆኖ የጥንት አባቶች የህዳር ወር ስያሜን ከጥንታዊው የባቢሎን ቋንቋ ወስደውታል። ይህ ካልሆነ ደግሞ በቸሃ ጉራጌ ህዳርን “ይዳር” ይለዋል። ስለዚህ ከውጭ ካላመጣነው ከራሳችን የጉራጌ ሴም ቋንቋ ተውሰነው ሊሆን ይችላል።
ታህሳስ – በግዕዝ ሐሰሰ ማለት፤ ተጓዘ ሄደ፤ ወይም አሰሰ እንደማለት ነው። የታህሳስ ወር ደግሞ ወታደሩም ነጋዴውም ከአገር ወዳገር የሚንቀሳቀስበት፤ የሚሄድበት፤ አገር የሚያስሥበት ወር ነው። ጉዞ ብሎ ተጓዘ እንደሚባለው… ሐሰሰ ብሎ ተሐሰሰ በመሆኑ፤ ተሃሰስ ወይም የጉዞ ወቅት ማለት በመሆኑ – ታህሳስ ቃሉን ያገኘው – ሀሰሰ ከሚለው ቃል መሆኑን መቀበል አይከብድም።
ጥር – በግዕዝ ጥሁር ማለት፤ ንጹህ ወይም ጥሩ ማለት ነው። የጥር ወር ሰብል ተሰብስቦ፤ ጥጋብ የሚመጣበት፤ ሰርግ እና ምላሽ፤ ድግስ እና ግብዣ የሚዘወተርበት ወር ነው። ለዚህም ነው – በግዕዝ ጥሁር፤ በአማርኛ ጥሩ ወይም ጥር የሚል ስያሜ ይዞ የቀረው። በሌላ በኩል ደግሞ – ለምሳሌ በጥንታዊው ደቡብ አረቢያ “ፀረረ” እና በጉራጊኛ – የጥር ወርን “ጥርር” በሚል ስያሜ ይጠሩታል። የዚህም መነሻ – በዚህ ወር ያለው ጠራራ ጸሃይ ሊሆን ይችላል። የጸሃይዋ መጥረር ወይም ማቃጠል አንደኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል – “ጥር” የሚለውን ስያሜ ያስገኘልን።
የካቲት – በግዕዝ ከቲት ወይም ይከትት ማለት፤ መክተት ከሚለው የአማርኛ ቃል ጋር አቻ ናቸው። በገበሬው ዘንድ እህል ተሰብስቦ ወደ ጎተራ የሚከተትበት ወር ነው። በመሆኑም የመክተቻ ወር መሆኑን ለማመልከት – የካቲት ተባለ። ከቲት ማለት ከታች ማለት ሲሆን፤ የካቲት ደግሞ የመክተቻ ጊዜ እንደማለት ነው።
መጋቢት – የመጋቢት ወር ፍቺ ግልጽ ነው። በግዕዙም ቢሆን… ምግብ የሚመግበውን መጋቢ፤ አንስታይ ጾታ ወይም ሴት ከሆነች ደሞ መጋቢት ይለዋል። ጥቅምት ጠቃሚ ወር በመሆኑ፤ ጠቃሚቷ ወር ጥቅምት ተብላለች። አሁን ደግሞ ምግብ ሰጪ እና መጋቢ የሆነውን ወር – መጋቢት ያሉት ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህ የበልግ ወር እህል እና ጥራጥሬ ብቻ ሳይሆን፤ ወፍ ዘራሽ እና የጫካ ፍራፍሬዎች ጭምር በየስፍራው ያድጋሉ። እንሰሳት እና አእዋፋትም እንደልባቸውና እንደሆዳቸው መጠን የሚመገቡበት ወር ስለሆነ፤ ይህን የምግብ እና የጥጋብ ወር መጋቢ ወይም መጋቢት ብለው ጠሩት።
ሚያዝያ – በአረብኛ – ማዛ ማለት መልካም ወይም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ሚያዝያን ከመልካም ሽታ ጋር ያያይዙታል። እውነታው ግን ወዲህ ነው። ሚያዝያ የሚለው ቃል የሚወለደው፤ “መሐዘ” ከሚለው የግዕዝ ቃል ነው። መሐዘ ማለት፤ ጎለመሰ ወይም ሚስት ለመያዝ በቃ ማለት ነው። እንደልማድ ሆኖ ከግንቦት ወር ጀምሮ ሰርግ አይደረግም። ስለዚህ የጎለመሰ ወይም የመሐዘ ሰው፤ ሚዜ አደራጅቶ ሚስት የሚያገባው ከግንቦት ወር ቀድሞ በሚገኘው ወር ነው። በዚህ ምክንያት ወሩም… ትዳር መያዣ ወይም መሐዘ – መሐዘያ – መያዥያ ሲባል ቆይቶ፤ አማርኛው ሚያዝያ ብሎ ቃሉን ወረሰው።
ግንቦት – ትርጉም እና አመጣጡ አማርኛ ነው። በዚህ ወር መሰረት ተቆፍሮ ግንባታ የሚጀመርበት ነው። ለምሳሌ ፈለገ የሚለው ቃል ፍላጎት እንደሚባለው፤ ሰረቀ ብሎ ስርቆት እንደሚባለው፤ ገነባ ብሎ ግንቦት ይላል። በአገራችንም በዚህ ወር በርካታ የግንባታ ስራዎች ይከናወናሉ። የአባይ ግድብ ጭምር የተጀመረው በግንቦት ወር ነው።
ሰኔ – የቃሉ ምንጭ ትግረ ትግርኛ ነው። በትግረ ሰነየ ማለት መልካም ሆነ፤ ሰናይ ሆነ፤ አማረ ማለት ነው። ይህ ወር በአርጎብኛም ጭምር ሰነይ ይባላል። አማርኛው በሂደት ቃሉን… ከሰነይ ወደ ሰኔ ቀየረና የዚህ ወር መጠሪያ አድርጎታል።
ሐምሌ – በሐምሌ ወር ክረምት ይገባና ልምላሜ ይጀምራል።  የለመለመ ነገር ደግሞ ሐመልማል ይባላል። ሐመለ ማለት አበባ አፈራ ማለት አይደለም፤ አበበ ወይም ለመለመ ማለት ነው። ሐምለይ ማለት ደግሞ ለምለም ማለት ነው። በስነ ቃል ብዜት… ሐመለ፣ ሐምለይ እያለ ይበዛል። ደቡብ አርጎባም ቢሆን፤ እንዳማርኛ ወሩን ሐምሌ ነው የሚለው። የሆኖ ሆኖ… ሐምለይም በጊዜ ሂደት ወደአማርኛው አጠራር ሐምሌ ተባለ። በትግርኛ ሐምለ፤ ጉራጌ አገር ደግሞ ክስተን፣ ስልጢ፣ ወለኔ፣ ሙኸር ሐምሌን አምሌ ይሉታል።
ነሃሴ – የነሃሴ ወርን አመጣጥ ከአረብ አገር የሚያደርጉ አሉ። በእርግጥ ግብጽ እና አረቦች የጳጉሜን ወር “ናሴ” ብለው ይጠራሉ። ሆኖም 12ኛ ወር ማለትም ነሐሴን ከአረቦች ወሰድን የሚለውን አልስማማበትም። በግዕዝ ነሐሰ ማለት መስራት እና መገንባት ነው። በአገራችን በነሐሴ ወር የሚገነባ ነገር ብዙም ስለሌለ፤ ከግዕዙ መጣ ለማለት ያስቸግራል። የነሃሴ ትክክለኛ አመጣጥ ሊሆን የሚችለው፤ በዚህ ወር በሰማይ ላይ የምናያቸው ነሃሳማ ቀለማት ናቸው። እዚህ ላይ ስለነሃስ ለማያውቁ ሰዎች ጥቂት ማብራሪያ እንስጥ።
ነሃስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለረዥም ጊዜ ይታወቃል። የቤተክርስቲያን ደቀል፣ መስቀል እና ጸናጽል ጭምር በነሃስ ይሰራል። ነሃስ ደግሞ በባህሪው እየቆየ ሲመጣ ቀለሙ ወደግራጫነት ይቀየራል። እጅግ ከበዙት የአለማችን ሃውልቶች መካከል የኒውዮርኳን Liberty of Statue መጥቀስ ይቻላል። በነጭነት እና በግራጫነት መካከል የሚገኝ ቀለም አላት። የነሃሴን ሰማይ ብንመለት፤ እንደአህያ ሆድ ነጭ፣ ግራጫ እና ጠቆር ብሎ እናየዋለን። እናም በኢትዮጵያ የነሃሴ ወር ሰማይ ነሃስ የመሰለ፤ ነሃሰይ የሆነ ነው። ነሃሰይ ማለት ደግሞ ነሃስማ ቀለም ማለት ሲሆን፤ አማርኛው ደግሞ ልክ ሰነይን ሰኔ፤ ሐምለይን ሐምሌ እንዳለው፤ ነሃሰይን ነሃሴ ብሎታል።
ጳጉሜ – እነዚህ 12 ወራት ወይም 360 ቀናት ካለቁ በኋላ፤ ሽርፍራፊና ቀሪ 5 ቀናት ይኖራሉ። እነዚህ ትርፍራፊ ቀናት በእንግሊዘኛው  epagomenal ኤፓጎሜናል ይባላሉ። በግሪክ ደግሞ ፓጉሜን ይሉታል፤ የግሪክ አቻ ትርጉም “የተረሱ ቀናት” ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ… እነዚህ አምስት ቀናት ያሉበትን የቀናት ጥርቅም አንድ ላይ አድርገው፤ 13ኛ ወር አድርገውታል። ቃሉንም ከግሪክ በመዋስ፤ ፓጉሜን ጳጉሜ ብለነዋል።

 

Sunday, September 8, 2024

መሸቀጫ ሆንሽ!!! አብራሃም ለቤዛ


 



መሸቀጫ ሆንሽ!!! አብራሃም ለቤዛ

 

ሰንደቅ አላማ  የሚጥሉሽ የሚያነሱሽ፤ 

የጭንቅ ቀን  ያስታወሱሽ

ሲፈለጉ የሚረግጡሽ፤

የሚበጥሱሽ፤

ያ ያየነው በመስቀል በዓል፤

በአድዋ ክብር በዓል፤

ፖሊስ ከካድሬ ተናቦ ሰንደቅ ዓላማ ሲያረክስ፤

ከመኪና ሰንደቅ ጌጥ ሲልጥ ሲያሻው በመቀስ ሲመቅስ፤

ዛሬ ስልጣን የሚያጣ መስሎት ፤

በእምየ ኢትዮጵያ ተከልልሎ፤

ሰንደቅ ሰንደቅ ሰንደቅ ዓላማየ፤

እንዴት ተደረጎ ይደፈራል ይላል ፤

ሰንደቅ ይዘምራል፤

ሰንደቅ ይንከባከባል፤ ይሰቅል ያወረዳል፤

እባክህን እባክሽን አታዋክቡን፤

እንደለመድከው  እንደለመድሽው የካድሬነት ወጉን ፤

ለሰንደቅ ዓላማ ስትጠሩን ፤

ምናለ ብታስታዉሱ የረገጣችኋትን፤

ሰንደቅ ዓላማዋን የረገጣችኋትን የመቀሳችኋትን፤

ከወጣቱ አንገት ከሚሞተው ከሰንደቅ ዓላማ በፊት፤

ከከበዎሮ ከዕምነት ተቋም ከሚተጉት በፀሎት ፍታት፤

ከቀሚሷ መቅሳችሁ እናት ባገር እንዳንመስል፤

ያስደፋችሁ የእናት አንገት የአገር ክብር፤

ይረሳል ወይ ድርጊታችሁ ለራሳችሁ፤

ካድሬም ሾርት ሚሞሪ ነው ለካን፡፡

 


Sunday, July 28, 2024

ኢትዮጵያዊው ሠማዕት፡-አቡነ ጴጥሮስ ስሜነህ ደስታ (ዘመን መጽሔት ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም )

 

 የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ታላቅ ሠማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በቀድሞ አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በፍቼ ከተማ ተወለዱ። አቡነ ጴጥሮስ በሠማዕትነት እንደሚሞቱ መምህራቸው በትንቢት ነግሯቸውም ነበር። አለቃ ተጠምቀ የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋር አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው ‹‹ሀይለማሪያም፣ አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚች አገር ላይ ይሰለጥናል። ታዲያ አንተ ያኔ በነፍስህ ሳትሳቀቅ በሠማዕትነት እለፍ። ሠማዕትነት ክፍልህ ነው። አደራ!›› ብለዋቸውም እንደነበር ይነገራል።

ይኸውም ትንቢት ደርሶ አቡነ ጴጥሮስ በሠማዕትነት ለማለፍ በቅተዋል። አቡነ ጴጥሮስ የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መምህር ሀይለማሪያም ይባሉ ነበር። በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሀይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል። የቤተክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በዋሸራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈፅመው መምህርም ሆነዋል። የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር በመሄድ

 ተምረዋል። በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጽሐፍት ሚስጢር ይመግቡ ወደ ነበሩት ወደ ሊቁ አካለወልድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጽሐፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትን እና ሊቃውንትን በሚገባ አካሂደዋል።

ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አማራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለዘጠኝ ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ። በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈፀሙ። ከዚያም በመምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለስድስት ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረጽዮን ቅድስተ ማሪያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል። በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግስት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንስሀ አባትም ሆኑ።

ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆች እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት በሀይማኖታቸውና በስነምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ። ከዚህ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምስራቀ ኢትዮጵያ ተብለው ተሹመዋል። ቤተክርስቲያንንና አገራችንን በፀሎታቸው፤ ሕዝብን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነት አውጆ ሕዝቡንም በግፍ ይገድል ጀመር።

አቡነ ጴጥሮስ ይህንን ግፍ በማየታቸው ከአገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በፀሎታቸው ሊዋጉት ተነሱ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ተከትለው ወደ ማይጨው ዘመቱ። ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ ጋዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሳ የኢትዮጵያ ሠራዊት ቢበታተንም ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረሊባኖስ ሄደው ለሀገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሰላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል። በደብረሊባኖስ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ የነበረውን የእነ ደጅአዝማች አበራ ካሳ አርበኛ ጦር እና በሸንኮራ በኩል መሽጎ የነበረውን የእነ ፍቅረማሪያም አርበኛ ጦር እንዲሁም በምዕራብ ይመራ ከነበረው የእነ ደጃዝማች አባነብሶ ጦር ሶስቱም በአንድ ጊዜ ወደ መሃል አዲስ አበባ በመግባት አዲስ አበባ ላይ ሰፍሮ የነበረውን ፋሺስት ለመውጋት ታቅዶ የነበረውን እቅድ በመረጃ ክፍተት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀረ።

መጀመሪያ የእነ ፍቅረማሪያም አርበኛ ጦር በኮተቤ አድርጎ የካ ሚካኤል ላይ ሲደርስ ተመትቶ ተመለሰ። ይሄኛው እንዳለቀ የእነ አባነብሶ ጦር በባቡር ጣቢያ መጣሁ ቢልም በጠላት ጦር ድጋሚ ተመትቶ ተመለሰ። መጨረሻ ላይ የእነ ደጃዝማች አበራ ካሳ አርበኛ ጦር በእንጦጦ በኩል ቢመጣም እሱም በጠላት ጦር ተመትቶ ተመለሰ። በዚህ አይነት ሁኔታ ሶስቱም የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደ መጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኞች ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም። ይልቁንም ብችል ጠላት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ እርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት ጠላት ላይ እንዲነሳ አደርጋለሁ። ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ። በማለት ከአርበኞቹ ተነጥለው አዲስ አበባ ቀሩ።

ይሁን እንጂ ጠላት በመላው ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አቡነ ጴጥሮስን እንዳሰቡት ሊያንቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር። በመሆኑም አቡነ ጴጥሮስ የሀገሬ ህዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሠማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑ። የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለነበረው ለራስ ኃይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡ። እሱም አቡነ ጴጥሮስን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. አሳልፎ ሰጣቸው። ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው።

አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሠማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት ኮሪየሬ ዲላ ሴራ የተባለ ጋዜጣ ወኪልና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፓጃሊ የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 በአዲስ አበባ በነበረበት ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈፀመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎት ነበር።

‹‹ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ። በዚህም ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው ለእስክድርያው መንበረ ፓትሪያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት። አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስ ህይወትን ለማትረፍ አስበው ነበር። ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስን የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብፅ ከአዲስ አበባ ውጪ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን ውስጥ እንዲፈፀም መመሪያ አስተላለፈ።››

የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ ፓጃሊ የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን ሲገልጽ ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረጅም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸውም ጠየም ያለ፣ አዋቂነታቸውና ትህትናቸው ከገፃቸው የሚነበብ ሲሆን በወቅቱ ለብሰውት የነበረው ልብስ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የቦካ ነበር።›› በማለት ይገልፀዋል።

በዚህ ሁኔታ ወደ ችሎት ቀረቡ። በችሎቱ የተሰየሙት ዳኞች ሶስት ሲሆኑ ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው። የመሃል ዳኛው ኮሎኔል ነበር። የቀረበባቸው ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር። ዳኛው ‹‹ካህናቱም ሆኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች፣ ሊቀጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ የጣሊያንን መንግስት ገዢነት አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ? ›› ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው። ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ አገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ›› አሉ።

በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ ‹‹አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሀይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፤ ስለውድ አገራችሁ፣ ስለቀናች ሀይማኖታችሁ ተከላከሉ። ነፃነታችሁን ከማርከስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ። የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪዪ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን›› ብለው አወገዙ።

ቀጥለውም አቡነ ጴጥሮስ ችሎቱ ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየፀለዩ ሕዝቡን ባረኩት። ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ አይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ። በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን አውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በወቅቱ ምንም ፍርሀት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረ ኢጣሊያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሀትም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር። የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ፀልይው በመስቀላቸው ባረኳቸው።

አቡነ ጴጥሮስ ሊገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሁ አስር ሜትር ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያው ተወሰዱ። ከገዳዮቻቸው አንዱ ‹‹ ፊትዎን መሸፈን ይፈልጋሉን ?›› ሲል ጠየቃቸው። ‹‹ይህ ያንተ ሥራ ነው›› ሲሉ መለሱለት። ወዲያው ቦታው እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ተደረጉ። ከዚያም ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ ተኩስ በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ነገር ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያ በኋላ አንድ ወታደር በሶስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው።

አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉበት ቦታ መሀል አዲስ አበባ ዛሬ መታሰቢያ ሀውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ፓጃሊ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሠማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል። በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ ? ሲል በወቅቱ አቡነ ጴጥሮስ ሠማዕትነት ሲቀበሉ በቦታው በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉት የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው ሲመልሱ፣ ‹‹ አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ እለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘው የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለው በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውን ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩስ ገደሏቸው። ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ህዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ። ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ‹በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል› አለኝ። ‹እንዴት? ›ብለው ‹አላየህም ሲያጨበጭብ !›አለኝ ‹ባታውቀው ነው እንጂ ሕዝቡ ሲናደድም ያጨበጭባል› አልኩት። እንዴት ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት። ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና የኪሳቸውን ሰዓት አሳየኝ›› ብለዋል።

አቡነ ጴጥሮስ ሠማዕትነትን በተቀበሉበት ቦታ ላይ የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸዋል። የእኚህን ታላቅና ቅዱስ ሠማዕት አባት ክብርና ተጋድሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ቅዱስ ሰማዕት ብሎ በማፅደቅ በስማቸው በቅድስና ማዕረግ በስማቸው ታቦት ተቀርፆ ቤተክርስቲያን እንዲሠራላቸው ወስኗል። ይህም በተወለዱበት በሰሜን ሸዋ ስላሴ ሀገረስብከት በፍቼ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኗል። ጉምቱ ባለቅኔ ፀጋዪ ገብረመድህን በግጥሙ ህያው አድርጓቸዋል። ይሁንና አፅማቸው የት እንደወደቀ ዛሬም ድረስ ሚስጢር እንደሆነ አለ። ደራሲ ፀሀይ መላኩ በአንድ ወቅት በኢቢኤስ ቴሌቭዥን ለብራና ልጆች ፕሮግራም በሰጠችው ቃለ ምልልስ የአቡነ ጴጥሮስ አስክሬን ፉሪ አካባቢ መኒሳ በምትባል ጉብታ ላይ ስለመቀበሩ የነገሯት አባት ስለመኖራቸው ተናግራለች።

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም መርጊያ አቡነ ጴጥሮስ ከህጻንነታቸው ጀምሮ ፆመኛና ፀሎተኛ እንደነበሩ እንዲሁም መንፈሳዊ ህይወት እንደሚታይባቸው፤ ዕድገታቸው በሀይማኖት ትምህርትና በመንፈሳዊ ህይወት የታጀበ እንደነበረ በመግለጽ ስለዕድገታቸው ያስረዳሉ። ከስጋዊው ይበልጥ መንፈሳዊው ህይወት ስለማረካቸው በፆም በጸሎት መወሰን ብቻ ሳይሆን፤ዓለም በቃኝ ብለው ምንኩስናን ተቀብለው በመምህርነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ በወቅቱ አልጋ ወራሽ በነበሩት በራስ ተፈሪ ተመርጠው ቅዱስ ቄርሎስ መጽሐፍን ወደ አማርኛ እንዲተረጉሙ ከተመረጡ አምስት ሊቃውንት መካከል አንዱ ሆነው መሥራታቸውን ይገልጻሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም አቡነ ጴጥሮስ ለጣልያን አገዛዝ ባለመሸነፍ በአደባበይ ሕዝብ በተሰበሰበበት በጥይት ተደብድበው መሞታቸው በመንፈሳዊው ዓለም ሠማዕት እንደሚያደርጋቸው ጠቅሰው፤ በሠማዕትነታቸውም ፍቼ ከተማ ላይ በስማቸው የተሰየመ ካቴድራል መኖሩን እና በቅጥር ግቢው ውስጥ አዲስ አበባ ከተማ ያለውን የሚመስል ሀውልት በመታሰቢያነት የቆመላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በፍቼ ከተማ ላይ በከተማ አስተዳደሩ በሰላሌ ኦሮሞ ማዕከል ውስጥ በስማቸው የተሰየመ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳለም ይገልጻሉ።

የአቡነ ጴጥሮስ ተጋድሎ ከጥቅምና ከማዕረግ በላይ ኢትዮጵያን ማስቀደም እንደሚገባ እና አገርን ከጠላት ለመከላከል ሀይማኖትም ሆነ ብሔርን ወይም ሌላ ነገርን ማዕከል አድርጎ መነሳት እንደማያስፈልግ የሚያሳይ ነው በማለት ረዳት ፕሮፌሰር ስዩም ያስረዳሉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ፀጋዬ ዘለቀ የአቡነ ጴጥሮስ የሠማዕትነት ተግባር በወቅቱ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያ መሞት ክብር እንደሆነ በማሳያነት የሚጠቅሱት መሆኑን እና የአርበኝነት ትግሉ እንዲፋፋም ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። በወቅቱ ለነበሩት ብቻ ሳይሆን የአሁኑም ሆነ የቀጣዩ ትውልድ የእሳቸውን ተግባር በማየት አገርን መውደድና ለአገር መቆም ምን እንደሚመስል ሊማርበት የሚያስችለው ነው ይላሉ።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም  


Friday, January 12, 2024

A reform culminated in changing logos

Abiy Administration in the name of reform, he is aggressively engaged in changing organization logos and in some case seems elimination of long held and accustomed logos that bear the lion.  A reform culminated in changing logos Abiy who claimed a master of all, call his log changing reform ergonometric that bring mood of employees hardworking and then he dragged the nation in to defaulted. An extravagant expenditure on non-strategic areas such as lavish palace to bring his mood of primer tenure.The argument by some institutions like federal police doesn't hold water

Ethiopian Federal Police - Posts | Facebook

Sunday, October 15, 2023

ኤርትራና ሲንጋፖር -አብራሃም ለቤዛ

 

 

ኤርትራና ሲንጋፖር
አብራሃም ለቤዛ
>><<>><<>><<>><<>><<>><<>><<>><<>><<>><<>>><<>><<>><<>><<>><<>><<
ኤርትራና ሲንጋፖር
አብራሃም ለቤዛ

ኤርትራ ከሲንጋፖር ጋር ለመተረክ የፈለግኩት ከሰሞኑን የኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ተቀማጭ አማባሳደር ከሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስተር  Mr. Yap Ong Heng ጋር ተገናኙና ተወያዩ የሚል ዜና ነው፡፡  ነገር ነገር ያነሳዎል እንዲሉ ለመተረክ የፈለግኩት ስለሁቱ አገሮች ግንኙነት ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፖር እንሆናለን ይል ስለነበረው የኤርትራዊያን ቅዠት ነው፡፡

የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵ ለመገንጠል በሚያደርገው ጥድፈት ዋዜማ ኤርትራን የምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፖር እናደርጋታል ይል ነበር፡፡  የየደቡብ ምስራቅ ኤሺያ አገሮች በአጭር ጊዜ ከድህነት ስለወጡ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች መቅኛ ነበሩ፡፡  ፈጣን እድገትና ልማት ግን ትክክለኛ  የፖሊሲ አቅጣጫ በመያዝ የሚመጣ እንጂ በማለም ብቻ የሚሆን አይደለም፡፡  የኤርትራዊን የምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፖር የመሆን ምኞት የመጣው ራሳቸውን ከሌላው ሀባሻ የኢትዮጵ ህዝብ እንዲሁም ከትግሬ ወንድሞቻቸው ለይተው ማየታቸው ነው፡፡ የ60 ዓመት የጣሊያን ቅኝ ገዢ ፖሊሲ በኤርትራዊያን ላይ ይኸ አስተሳሰብ እንዲጫን አድረጎል፡፡ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ “Ethiopia and Eritrea- The Federal Experience”  በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ ለመነጠል ዳግም የሄዱበት መንገድ እኛ የተለየን ነን ፤ ከሃበሻ እኛ የሰለጠንን ነን፤ እኛ ከተገነጠልን በፍጥነት እንበለፅጋለን የሚለው አስተሳሰብ ስለሰረፀባቸው ነው ይላል፡፡

የሆነው ግን ኤርትራ የአፍሪካ ሲንጋፖር ሳይሆን የአፍሪካ ሰሜን ኮርያ ሆነ፡፡ የሃበሻ ምቀኝነት እንዲሉ ለዚህ ደግሞ የወያኔ ኢተዮጵያ ኤርትራን በማሳጣት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡

የደቡብ ምስራቅ ኤሽ አገሮች ሲንጋፖር ፤ ማሌዥያ፤ ቬትናም፡ታይላድ ፤ኢንዶኔዢያና ፊሊፒንስ ሲሆኑ ፤ በአጭር ጊዜ ከድህነት በመውጣታቸው ምክንያትም የኤሽያ ታይገር የሚል የዳቦ ስም ወጥቶላቸዋል፡፡  የወያኔዎ ኢትዮጵያ ልማታዊ መንግስትን በመከተል የደቡብ ምስራቅ ኤሽያ አገሮች መንገድ እከተላለሁ ብትልም፤  ነገር ግን የኢትዮጵያ ፖሊሲ በጎሳ ፖለቲካ ፤ የጋራ መግባባት የሌለው ፖለቲካ ሃይል እና በሙስና የተጨማለቀ ፖለቲካ ሃይል የተተበተ ስለሆነ የደቡብ ምስራቅ ኤሽያ አገሮችን ፈለግ መከተል አልቻለችም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለራሷ የአፍሪካ ላይዮን የሚል የዳቦ ስም አውጥታለች፡፡ ለከታታይ 14 ዓመት (2005-2019)  በሁለት ዲጂት ያደገ ኢኮኖሚ ባለቤት የሚል የተለመደ የወያኔዎች የአፍ ማሞሻ ጥቅስ ነበር፡፡

ፅንፈኛው ጃ-War  መሃመድ   የኦሮሞ ፖለቲከኛም በሲንጋፖር ኢኮኖሚ እምርታ እንደሚማረክና ሲንጋፖር እየተማረ

የሲንጋፖርን እድገት እናዳጠናዉም በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡ ችግሩ የሲንጋፖርና የደቡብ ምስራቅ ኤሽያ አገሮች ሲንጋፖር አገሮች መመንደግ ሳይሆን እነሱ የሄዱበትን  እኛ እንዳንሄድበት  ራሳችንን አድርገናል፡፡ የእኛ መንገድ ማለት በህገመንግስታችንም ሆነ በኢኮኖሚ ፖሊሲያችን ኢትዮጵያዊነት በዜጋነት እንዲደራጁ አንፈቅድም፡፡  የብሄር ፖለቲካ ይዘን እንደ ዝንጀሮ መንጋ ባለች ሃብት (ክምር) ላይ ሰፍረን መበዝበዝ እንጂ ምርታማነትና ዕድገትን አናመጣም፡፡

ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዲሉ የአፍሪካ ፖለቲከኞች ፊት ለፊት ያገጠጠ ፖለቲካ ችግራቸውን ከመጋፈጥ ይልቅ የጦስ ዶሮ መፈለግ ይዘዎል፡፡ አዎ ላላማደጋችን ወደብ-አልባ አገር መሆናችን ትለቅ አስተዎፅኦ አለው ነገር ግን አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ የበለጠ አሳሳቢ ጉዳያችንን መፍታት አልቻልንም፡፡ አገርን ሰላም ማድረግ መንግስት አልቻለም፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት አልቻሉም፡፡

ብልፅግና መራሹ ፤ የኦሮሞ ፅንፈኞች ከዚህ መማር ቢችሉ ኢትየጵያዊያንን በአንድ ማስተባበር አለባቸው፡፡ ብቻቸውን ግን ቀይ ባህር ፤ ህንድ ውቅያኖስ የሚሉት አያዋጣውም፡፡ ሻብያና ኦነግ ከ30 ዓመት በፊት በአንድ ሰርተዎል ፤ አሁን ደግሞ አንዱ የጣለውን መንገድ አንዱ እያነሳ ባለህበት እርገጥ ሆኖል፡፡

Wednesday, August 30, 2023

የኦሮሞ ብሔርተኞች ተቃርኖ [Hypocrisy]! – አቻምየለህ ታምሩ

 የኦሮሞ ብሔርተኞች ተቃርኖ [Hypocrisy]! – አቻምየለህ ታምሩ

በኢትዮጵያ ምልሰት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራችውን የኦሮሞ ጀግኖች እንደ ኦነግ ያዋረደ ድርጅት የለም። በቤተ ኦነግ የጀግኖቹ ጀግና፣ የራሶቹ ራስ የራስ ጎበና ስም ስድብ ነው። እኛ ከፍ ስናደርጋቸው እነሱ ዝቅ ሲያደርጓቸው የኖሩትን የኢትዮጵያ ጀግኖች እፍረተ ቢሶቹ ኦነጋውያን ዛሬ ስማቸው ሳይጠራ የኖሩ ኦሮሞዎች አድርገው ለመተረክ ይቃጣቸዋል። ብሔርተኞቹ ነውረኞች ስለሆኑ በንጉሡ ስር የአድዋ ዘመቻ ጠቅላይ ጦር አዛዥ የነበሩትን የራስ መኮነንን መታሰቢያ ሐውልት በቅርቡ በሐረር ከተማ አናታቸው ይፍረስና ማፍረሳቸውን እንኳ የረሳነው ይመስላቸዋል።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ጀግኖችን አስተዋጽኦ ከኦነግ በላይ የረሳና ያዋረደው ማነው? ከኦነግ በተጨማሪ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ብሔርተኞች አይደሉምን? አገራቸው ያቆመችላቸውን ሐውልትና ስም የደመሰሱ እነዚህ ነውረኞች አይደሉምን?

በክርስትና ሃይማኖት የቤተ ክርስቲያን መሰረት የሚባሉ አራት ጉባኤዎች አሉ። ቤተክርስቲያን የፀናችው በነዚህ አራት ጉባኤዎች ነው ተብሎ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ይታመናል። ይህንን framework በመጠቀም በ1927 ዓ.ም. ከዛሬ 84 ዓመታት በፊት የጎጃሙ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ራስ ጎበናን የኢትዮጵያን ምልሰት ካቆመው አራቱ ጉባኤ መካክል አንዱ ያደርገዋል። በወቅቱ የነበረው የመንፈስ ድክመት አገራችንን አደጋ ላይ ቢጥላት ኢትዮጵያ ምህርት ወይንም መዳን ታገኝ ዘንድ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ የጠራው የኢትዮጵያ ብርታት የቆመበትን የነራስ ጎበናን መንፈስ ነበር። እንዲህ ሲል. . .

አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናን ከሸዋ አሉላን ተትግሬ፤
ስመኝ አድሬአለሁ ትናንትና ዛሬ፣
ጎበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ፤
****
ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣
አሉላ ከትግሬ ጎበና ከጋላ፤
ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፤
አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ፤
***
[የኔ ራስ] ጎበና ከፈረስህ ጋራ ተነስ እንደገና፣
ትምህርት እንዲስፋፋ ጉልበት እንዲጠና፣
አራቱ ጉባኤ ይነሱልንና፣
መኮንን ደረሶ አሉላ ጎበና፣
አገራችን ትማር አሁን እንደገና፤
[የኔ ራስ]ጎበና ከፈረስህ ጋራ ተነስ እንደገና።

በዚህ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ገድልና ጀብዱ ላይ የሸፈቱት ኅሊና ቢሶች ኦነጋውያንና የርዕዮታለም መንትዮቻቸው ናቸው። የእነ ራስ ጎበናና የተቀሩት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችን አገርና ታሪክ ለማፍረስ እነ ኦነግ ሞቃዲሾ ሲከትሙ፣ እነ ኢሕአፓ ወደ አሲምባ ሲኮበልሉ፣ እነ ሕወሓት ደደቡት ሲወርዱ የራስ ጎበናንና የሌሎችን ኢትዮጵውያን ጀግኖች አርበኞች ታሪክ ጠብቆ ያቆየው እንደ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ አይነቱ አማራ ነው።

ዐፄ ዮሐንስ ምንም እንኳ ጎጃምና ወሎን ቢጨፈጭፉም መተማ ላይ ሰማዕት በመሆናቸው አማራው የሚያከብራቸውን ያህል በፋሽስት ወያኔዎች ዘንድ ክብር የላቸውም። አማራው መተማ ዮሐንስ የሚል ከተማ በስማቸው ሲጠራ ፋሽስት ወያኔዎች ግን በባለሟላቸው በራስ አሉላ ስም የተሰየመውን ትምህርት ቤት የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ደደቢት በወረደው መለስ ዜናዊ ስም ለውጠውታል።

የኦሮሞ ብሔርተኞች ከሰሞኑ የአድዋን ድል ዋነኞቹን የጦሩ አዛዦችን ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክንና እቴጌ ጠሐይቱን ትተው የኦሮሞ ጀግና ፈረሰኛ ወታደሮች ድል እንደሆነ አድርገው እየተናገሩ ናቸው። እንደሚታወቀው የአድዋ ጦርነት ጥሊያን የተጨፈጨፈበት ድል ነው። የኦሮሞ ብሔርተኞች እየነገሩን ያለው ይህንን የጥሊያን ጭፍጨፋ ያካሄዱት የኦሮሞ ፈረሰኛ ወታደሮች ናቸው የሚል ነው። ጥሩ። ይህንን የሚሉትን የኦሮሞ ብሔርተኞች አኖሌና ጨለንቆ ላይ ተካሄዱ ለሚሏቸው ጦርነቶች ተደረገ ለሚሉት ጭፍጨፋ ግን ኃላፊነቱን የዳግማዊ ምኒልክ ያደርጉታል።

በታሪክ ሞቅ ሲል በማንኪያ፤ ሲቀዘቅዝ በእጄ አይሰራም። በአድዋ ድል የኦሮሞ ፈረሰኛ ወታደሮች ከሆነ የአርሲና የሐረር «ጭፍጨፋ» የተባለውንም የፈጸሙት እነዚህ የአድዋ ድል ባለቤት የተደረጉት ጀግና የኦሮሞ ፈረሰኛ ወታደሮች ናቸው። ለአድዋው ድል ሲሆን እውቅናው ከሁሉ በላይ ለጀግና የኦሮሞ ፈረሰኛ ወታደሮች፤ እነኚህ ወታደሮች አርሲና ሐረር ባካሄዱት የማስገበር ዘመቻ ደረሰ ለሚባለው «ጭፍጨፋ» እና «ቅኝ ግዛት» ግን ተጠያቂው ዳግማዊ ምኒልክ ሊሆኑ አይችሉም!

«ሰውን ሲወዱ ከነንፍጡ እና ልጋጉ ነው» ይላል ያገሬ ሰው። በአድዋ ላይ የተመዘገበውን ድል ከሁሉ በላይ የኦሮሞ ጀግና ፈረሰኛ ወታደሮች የሰጠ አንድ ሰው፤ ከአድዋው ድል ጥቂት አመታት በፊት እነዚሁ የኦሮሞ ፈረሰኛ ወታደሮች በአርሲና ሐረር ያደረሱትን «ጭፍጨፋም» የራሱ ወገን የሆኑ ሰዎች ያደረሱት መሆኑን አምኖ ትክሻውን ደልደል በማድረግ መቀበልና ተፈጸመ ላለው ጭፍጨፋም ተጠያቂ ማድረግ ካለበት እነሱኑ ነው እንጂ ሌላ አካል ተጠያቂ ማድረግ የለበትም።

ስለዚህ ዛሬ የኦሮሞ ብሔርተኞች በአድዋው ድል እውቅና እየሰጧቸው ያሉት የኦሮሞ ፈረሰኛ ወታደሮች ከአድዋ ድል ጥቂት አመታት በፊት እነዚሁ የኦሮሞ ወታደሮች ሐረርና አርሲ ላደረሱት «ጭፍጨፋ» እና «ቅኝ ግዛት» ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ተጠያቂ የሚሆኑበት አመክንዮ ሊኖር አይችልም! ስለሆነም ወይ የአድዋውን ድልም እንደ አኖሌውና ሐረሩ ጭፍጨፋ ሁሉ ለምኒልክ ተውት አልያም በነዚሁ አድዋ በዘመቱ የኦሮሞ ጀግና ፈረሰኞች የተካሄደውን የአርሲና የሐረሩ ጭፍጨፋ ያላችሁትንም እንደ አድዋው የጥሊያን ጭፍጨፋ ሁሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ተጠቃለሉትና ምኒልክን ለቀቅ አድርጓቸው  Otherwise it is pure hypocrisy to make such a sudden U-turn 213

Tuesday, June 6, 2023

በካራማራ ታንክ ማራኪው ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ (ካራማራ የኢትዮጵያውያን የድል ቀን (ዳግማዊ ዓድዋ) ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ)

       ካራማራ የኢትዮጵያውያን የድል ቀን (ዳግማዊ ዓድዋ) ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ








ካራማራ የኢትዮጵያውያን  የድል ቀን (ዳግማዊ ዓድዋ)

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ
 
እንደ መግቢያ 
  በ1950ዎቹ መጀመሪያና አጋማሽ ላይ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡባቸው አመታት ነበሩ ። የጣሊያን ሶማሊ ላንድና የብሪቲሽ ሶማሊላንድም በ1952 ነፃ ወጡና የሶማሊያን ሪፐብሊክ መሠረቱ ።
  ቀጥሎም ባለ 5 ኮከብ ያለው ባንዲራ አስተዋወቁ ። ትርጉሙም በኢትዮጵያ ፣ በኬንያ ፣ በጅቡቲ እና ሪፐብሊክ በመሠረቱት ሁለቱ ሶማሊላንዶች የሚገኝ መሬት የሶማሊያ ነው የሚል የታላቋ ሱማሊያ ህልም የሚያመለክት ነበር ።
  ከኢትዮጵያ ሉአላዊ መሬት ላይም አጠቃላይ ሐረርጌን ፣ ባሌን ፣ አርሲን ሲዳማንና ከፊል ሸዋን ለመጠቅለል የሚያስችል አዲስ ካርታ አዘጋጁ ።
  ጅቡቲና ኬንያ በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ለጊዜው እነሱን በመተው ነፃ ሀገር በነበረችው ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ የሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ይፈፅሙ ጀመር ። ኦብነግና ኦነግን የመሣሠሉ ተገንጣይ ቡድኖችን በማቋቋም የእጅ አዙር ጥቃትን አፋፋሙ ።
  ሶማሌዎች በ1953 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተከሰተውን የታህሳስ ግርግርን ተከትለውና በ1956 ዓ.ም. ላይ ከደፈጣ ጥቃት ወደ መጠነ ሰፊ የወረራ ሙከራ አደረጉ ። ሆኖም በጊዜው ቀጠናውን ይጠበቅ በነበረውና በጀግናው ሌ/ጀ አማን ሚካኤል በሚመራው 3ኛው አንበሳ ክ/ጦር ክፋኛ ተመትቶ ተመለሡ ።
   በ1962 ዓ.ም. ወታደሩ ጀነራል መሀመድ ዚያድባሬ በመፈንቅለ መንግስት የሶማሊያን መንግስት በትረ ስልጣን ተቆጣጠሩ ። የታላቋ ሶማሊያ ህልማቸውንም በይፋ ገልፀው ወታደራዊ ዝግጅታቸውን አጧጧፉት ። የመንግስታቸው ርዕይቶ አለምም በይፋ ሶሻሊዝም መሆኑን አወጁ ።
  በውጤቱም ከሶቪየት ህብረት በገፍ ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቅና ወታደራዊ ኃይላቸውን ለተከታታይ 7 አመታት ማፈርጠም ቀጠሉበት ። በውጤቱም 7 እግረኛ ክፍለ ጦር ፤ 600 ታንኮችን እና ሌሎች የያዘ 4 ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር እንዲሁም 70 አውሮፕላኖችን የያዘ ግዙፍ የአየር ኃይል ገነቡ ።
  በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሌላ የታሪክ ሂደት ላይ ነበረች ። የየካቲት 1966ዓ.ም. አብዮት ተከትሎ ቀኃሥ ከዙፋን አውርዶ መስከረም 2 /1967 ዓ.ም. ስልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊው ደርግ በበርካታ ጉዳዬች ተጠምዶ ነበር ።
  በሰሜን ነፍጥ አንስቶ የሚታገለው ሻእቢያና ጀብሃ ከአሥመራ ፣ ከፊል ምፅዋና ባሬንቱ በስተቀር ቀሪውን የኤርትራ ክ/ሀገር ተቆጣጥረው ነበር ።
  ኢዲዩ በጎንደር ፤ ህወኃትም በትግራይ መንግስትን በመፋለም ላይ ነበሩ ። በመሃል ሀገርና በሌሎች አከባቢዎችም ኢህአፓና ደርግ በነጭ ሽብርና በቀይ ሽብር ደም ይፋሰሱ ነበር ።
  ተቀናቃኝ ሀይሎቹም በመንግስት ላይ የሚፈፅሙት ጥቃት አልበቃ ብሏቸው ሶማሊያ የምታደርገው ጦርነት ልክ ነው ፤  አድሃሪ ጦርነት የሚያደርገው ደርግ ነው በማለት ሻእቢያ ፣ ህወኃት ፣ መኢሶን ፣ ኢህአፓ ፣ ኦነግ እና ጀብሃ የፕሮፓጋንዳ ድጋፋቸውን ለሶማሊያ ይሰጡ ነበር ።
በውጤቱም ኢትዮጵያ እጅግ ተዳክማ ነበር ።
    በአጠቃላይ ዚያድባሬ ያንን ሁሉ ግዙፍ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ የኢትዮጵያን የመንግስት ስልጣን የያዘው ደርግ ግን ከንጉሱ የተቀበለው 4 ክፍለ ጦሮች ብቻ ነበሩት ።
  እነርሱም 1ኛ ክ/ጦር (ክቡር ዘበኛ ) ፤ 2ኛ ክ/ጦር ኤርትራ የነበረው ፣ 3ኛ ክ/ጦር ምስራቅ (ኦጋዴን) የነበረው እና 4ኛ ክ/ጦር ደቡብ ነገሌ/ቦረና የነበረው ናቸው ። ከነዚህ ውጭ ተጨማሪ ኃይል አሠልጥኖና አስታጥቆ ወደ ሰራዊቱ አልጨመረም ነበር ።
   የጦርነቱ ውጥረት እያየለ ሲመጣ የተለያዩ የማሸማገል ጥረቶች በተለያዩ አካላት ቀጥለው ነበር ። የመጨረሻው የፊደል ካስትሮ ደቡብ የመን ኤደን ላይ ለማሸማገል ያደረጉት ጥረት በዚያድባሬ እብሪት ምክንያት ከሸፈ ።
  ፊደል ካስትሮም በዚያድባሬ መጠን ያለፈ ንቀት እጅግ ተቆጡ ፤ በአለማቀፍ ህብረተሰባዊነት መርህ መሠረትም ኢትዮጵያንም ማገዝ እንዳለባቸው ወሰኑ ። እያንዣበበ ያለው የመወረር አደጋ ያሰጋቸው የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም. በብሔራዊ የቴሌቭዢን ጣቢያ ብቅ ብለው ታሪካዊውን የእናት ሀገር ጥሪ መልእክት ለህዝባቸው እንዲህ በማለት አስተላለፉ ። ሀገርህ ፣ ህልውናህን እና አብዮትህን አድን ፤  ተነስ ! ታጠቅ ! ዝመት ! እናሸንፋለን ! ብለው ተናገሩ 
  የእናት ሀገር ጥሪውን ተከትሎ ከአራቱም የኢትዮጵያ መአዘናት ለሀገሩ ሉኣላዊነት ቀናኢ የሆነው ህዝብ በገፍ ወደ ታጠቅ ማሰልጠኛ ጣቢያ ተመመ ።
  በመጀመሪያ የከፋ ክ/ሀገር ዘማች ሚሊሻ ቀጥሎ የጎጃም ክ/ሀገር ሚሊሻ እያለ ወደ 300,000 ሺህ የሚጠጋ ህዝባዊ ሰራዊት ለስልጠና ታጠቅ ከተመ ። ታጠቅ አዲስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ነበር ።
  300,000 ለሚሆነው ሰልጣኝ የሚበቃና የሚመች መሠረት ልማት አልነበረውም ። ታጠቅ በቂ መጠለያ ፣ በቂ ማብሰያ ፣ በቂ መፀዳጃ ፣ በቂ ጠመንጃና ፣ … አልነበረውም ። ወቅቱም ዝናብ ይጥል ስለነበር የጭቃው ነገርም ለስጠናው ስራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር ።
  ከሀረር የጦር አካዳሚና ከሆሎታ ገነት ጦር ት/ቤት ስልጠና ላይ የነበሩት እጩ መኮንኖች ትምህርታቸውን አቋርጠው ከሌሎች የጦር ክፍሎች ከተውጣጡ አሠልጣኞች ጋር በመሆን ሰልጣኝ ህዝባዊ ሰራዊቱን ለማሠልጠን ታጠቅ ከተቱ ።
  የእናት ሀገር ጥሪው የተቀበለው የአዲስ አበባና የአከባቢው ህዝብም ዘማች ሚሊሻውን ሊደግፍ ወደ ታጠቅ ተመመ ። የእድር ድንኳኖች ፣ የማብሰያ ድስቶች ፣ የመመገቢያ ሰሀኖች ፣ የመጠጫ ኩባያዎች ፣ …በገፍ ወደ ታጠቅ ተጫኑ ። እናቶች በዓድዋው ዘመቻ የፈፀሙትን ገድል ለካራማራም ደገሙት ።
 በወቅቱ በኢህአፓ የሚደረገውም አፍራሽ ፕሮፓጋንዳና ማስፈራሪያ ሳያስፈራቸው ወደ ታጠቅ አቀኑ ።
በጉዟቸው ላይም
ማን ይፈራል ሞት
ማን ይፈራል
ለእናት ሀገር ሲባል …
በማለት የነሱንም ፣ የዘማቹንም ወኔ ያበረቱት ነበር ።
  በስራቸውም በፈረቃ ለሠልጣኙ እርጥብ ምግብ ያዘጋጃሉ ። ሚሊሻው ወደ ግንባር ይዞት የሚሄደውን ደረቅ ስንቅ ይቋጥራሉ ። ወንዶችም በፊናቸው እንጨት ይፈልጣሉ ፣ ውሃ ይቀዳሉ ፣ የሰልጣኙን ልብስ ያጥባሉ ።
  ኢትዮጵያ የቶሎ ቶሎ ስልጠናውን በተያያዘችው ወቅት ለተከታታይ 10 አመታት ሲሰለጥንና በገፍ ሲታጠቅ የነበረው የዚያድባሬ ሀይል ሐምሌ 3 ፤ 1969 ዓ.ም ላይ በሰፊው የኦጋዴን ክልል ላይ በርቀት ነጥቦች ላይ ተራርቀውና እርስበእርስ ለመረዳዳት በማይችሉበት ሁኔታ የነበሩትን የ3ኛ ክ/ጦር አካል የሆኑትን የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊቶችን የተለያዩ ክፍሎችን መግፋት ጀመረ ።
  የኢትዮጵያ ሰራዊት የሚቻለውን መከላከል ቢያደርግም በነበረው ከፍተኛ የኃይል አለመመጣን ምክንያት ሰራዊቱ እየጣለና እየወደቀ ለማፈግፈግ ተገደደ ። ሶማሊያም ገላዲን ፣ ቀብሪደሃር ፣ ደጋሀቡር ፣ ጎዴ ፣ ሙስታሂል ፣ አይሻ/ደወሌ ፣ ገርባሳ ፣ ጭናቅሰን ፣ …የሚገኙ የሠራዊት ክፍሎችን በመግፋት በምስራቅ 700ኪ.ሜ ፤ በደቡብ 300 ኪ.ሜ. ጠልቃ በመግባት የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት በኃይል ተቆጣጠረች ።
   ጅጅጋን ተቆጣጥረው የሀረርና ከተማ በመድፍ ቀለበት አስገብተው መደብደብ ተያያዙት ፤ የድሬዳዋም ከተማ አፍንጫ ስር ደረሡ ።
ሶማሊያ በተቆጣጠረችው አከባቢ የሚኖረውን ህዝብ በዚያድባሬ ሃይል የባርነት ቀንበር ስር ወደቀ ። ንብረት ወደ ሞቃዲሾ ተጋዘ ። ሴቶች ተደፈሩ ። በርካታ ሰላማዊ ዜጎችም በግዞት ወደ ተለያዩ የሶማሊያ ከተሞች በገፍ ተጋዙ ።
  በወቅቱ ሶማሊያ እጅግ ዘመናዊውን ስታሊን ኦርጋን (BM ) ጨምሮ አይነተ ብዙ ሩስያ ሰራሽ የጦር መሳሪያ ታጥቅ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በብዛት የታጠቀችው አሜሪካ ሰራሽ መሳሪያ ነው ።
   በጊዜው የኢትዮጵያ ትጥቅ ከሶማሊያ ጋር ሲነፃፀር ኃላቀር የነበረ መሣሪያ ነበር ።
   በወቅቱ  የጂሚ ካርተር ይመራ የነበረው የአሜሪካ አስተዳደር በቀኃሥ ዘመን የተፈፀመውን የተከፈለበት የጦር መሳሪያ ግዢ ውል እንዳይፈፀም በማገዱ ኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ ላይ ወድቃ ነበር ።
  ኢትዮጵያም የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ምስራቁ የሶሻሊስት ጎራ ፊቷን አዞረች ። በታህሳስ 1968 ዓ.ም ሶሻሊዝምን በማወጅ አጋርነቷን አሳይቷ ስለነበር ከምስራቁ አለም አመርቂ ድጋፍ ማግኘት ጀመረች ።
  ሶቪየትም ከሶማሊያ ጋር መቃቃር ስለጀመረች ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር በብዛት የጦር መሣሪያ ድጋፍና የባለሞያ /አማካሪዎች እገዛ አደረገች ።
  እጅግ ፈታኝ ስራ ቢሆንም ኢትዮጵያ ሰራዊቷንም ከአሜሪካ ሰራሽ መሣሪያ ስርአት ወደ ሶቪየት መሣሪያ ስርአት ሽግግር በሚያስደንቅ ፍጥነት አካሄደች ።
  ታጠቅ ጦር ሰፈር ሲሰለጥን የከረመው ህዝባዊ ሰራዊትም በሀገራዊ ወኔና በስልጠና ታግዞ ከኮሪያ የመጣ ሬንጀር ፋቲግ ለብሶ ለሰኔ 18 ለአደባባይ ሰልፍ ትርኢት ተዘጋጀ ።
  በእለቱም የነበረው የሰልፈኛው ሰራዊት እርዝማኔ በአለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በጣም ረጅም ነበር። ጫፉ መስቀል አደባባይ ሆኖ መጨረሻው ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፍያ /ጦር ኃይሎች ይደርስ ነበር።
  በወቅቱ ሰልፉን ይታዘቡ የነበሩ የተለያዩ ሀገሮች ታዛቢዎች እና ወታደራዊ አታሼዎች የደማቁን ሰልፍ እና የሰራዊቱን ብዛት በመጠራጠርቸው ከመነሻ እስከ መድረሻው በሂሊኮብተር ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ነበር ያመኑት ።
  በመስቀል አደባባይ የተገኘዉም ህዝብ ለሰራዊቱ ይሰጥ የነበረው ሞራል እጅግ አስደማሚ ነበር።  ህዝባዊ ሰራዊቱም ይህን ዜማ እያዜመ ለሀገሩና ለክብሩ መስዋዕት ለመሆን መዘጋጀቱን በከፍተኛ ወኔ ገለጸ።
ለአንድነቱ
ድሉ እንዲሰምር የነፃነቱ
ወጣ ወረደ : ሄደ ነጎደ ሠራዊቱ ::
አለኝ አደራ
የተቀበልኩት :ከጀግኖች አውራ
እንድትኖር : ሀገሬ ታፍራ ተከብራ
ብሎ ተነሳ : ህዝባዊው ሰራዊት
  ጉዞ ጀመረ
  እየዘመረ
እንዲያበራ
የነፃነት ድል : የአንድነት ጮራ
አውለበለበ የድል በንዲራ
                        እንዲያበራ ::
………….
ሀገሬ
መመኪያ ክብሬ
አትደፈርም ዳር ድንበሬ
ነፃነቴ
ውርሱ የአባቴ
ተደፍሮ ማየት : አልሻም መብቴ
ብሎ ነጎደ : ህዝባዊው ሠራዊት
                                  ጉዞ ጀመረ
                                   እየዘመረ ” …
ህዝባዊ ሰራዊቱም በ9ኝ ክፍለ ጦሮች ተዋቅሮ 8ኛ፣ 9ኛ ፣ 10ኛ እና 11ኛ ክ/ጦሮች እየፈከሩና እየሸለሉ ወደ ምስራቅ ዘመቱ ። 12ኛ ክ/ጦር ወደ ደቡብ ዘመተ ። 14ኛ ፣ 15ኛ ፣ 16ኛ እና 17ኛ ክ/ጦሮችም ወደ ኤርትራና ትግራይ ተላኩ ።
  በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አቅምም በፊት ከነበራት 4 ክ/ጦር ታጠቅ የሠለጠነው 9ኝ ክ/ጦር ሲጨመርበት የሰራዊቷ አቅም ወደ 13 ክፍለ ጦሮች አደገ ።
  የሶሻሊስት ኩባ ፕሬዝደንት ጓድ ፊደል ካስትሮም አንጎላ ከነበረው ሰራዊታቸው 18,000 ያህል የእግረኛ ተዋጊና የሜካናይዝድ ኃይል ከህክምና ባለሞያዎች ጋር በጀነራል ኦርላንዶ ኦቾዋ አማካይነት እየተመራ ወደ ኢትዮጵያ ኢንዲንቀሳቀስ አዘዙ ።
  ደቡብ የመንም እስከ 2000 የሚደርስ ጠንካራ የመድፈኛ ብርጌድ ድጋፍ አደረጉ ። ሶቪየት ህብረትም በማርሻል ፔትሮቭ የሚመራ ልዩ ልዩ የአማካሪ ቡድን ላከች ።
  ኢትዮጵያ 300,000 ሚሊሻ በአጭር ጊዜ አሰልጥና ከማስመረቋ በፊት ሶማሊያ ወረራ በካሄደችበት ወቅት ለንፅፅር ይጠቅም ዘንድ የኢትዮጵያና የሶማሊያ አጠቃላይ የጦር አቅም ንፅፅር ይህን ይመስላል ።
                                        ሶማሊያ            ኢትዮጵያ 
ሀ/ እግረኛ ክ/ጦር               8                      4
ለ/ ኮማንዶ ብርጌድ             4                      0
ሐ/ ሜካናይዝድ ክ/ጦር     4                      0
መ/ታንከኛ ብርጌድ              4                      1
ሠ/ BM /ስታሊን ኦርጋን      125                  1
ረ/ ታንክ                                608                  132
ሰ/ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ    253                  51
ሸ/ ተዋጊ አውሮፕላኖች          65                    8
  በመቀጠል በከፍተኛ እልህና ቁጭት የተሞላው ህዝባዊ ሰራዊት ከመደበኛ ጦሩ ጋር በመቀላቀል በታጠቀው ሀገራዊ ፍቅርና ወኔ ታግዞ በበርካታ ግንባሮች ተሠልፎ ነባሩን ጦር በማጠናከር የሶማሊያን ተጨማሪ መስፋፋት መግታት ጀመረ።
  በጀግንነት ጥሎ መውደቅ ተያያዘው ። ይህም አልበቃ ብሎት በዘመች ሚሊሻ አማካይነት በነፍስ ወከፍ መሳሪያ እየታገዘ የሶማሊያን ታንኮች በአስደናቂ ጀብድ ይማርክ ገባ።
  በወረራ ከተያዘው ህዝብ ጋርም እየተባበረ የሶማሊያን ወራሪ ማርበድበድ ተያያዘው ። ይህ ሀገርን ከወረራ ለማዳን ርብርብ በሚካሄድበት ወቅትም ከመነሻው የሶማሊያን ወረራ ደግፎ  የቆሙ እንደ ኢህአፓ አይነት ሃይሎች በጦሩ ውስጥ አስርገዉ ባስገቧቸው ኃይሎች ርብርብ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያን ሰራዊት በሚያሳዝንን በሚያሳፍር መልኩ ከኋላ ይወጉት ነበር ።
  በጣት የሚቆጠሩ አውሮፕላኖችን ግን እጅግ የበቁ አብራሪዎቹን የያዘው ጀግና የኢትዮጵያ አየር ኃይልም አለምን ባስደመመ የመዋጋት ብቃቱ በቁጥርና በዘመናዊነት የሚበልጡትን የሶማሊያን ሚጎች በአየር ላየር ውጊያ ከሰማይ ወደ መሬት እንደ ዝናብ ያራግፋቸው ጀመር።
  በአጭር ጊዜ የሶማሊያን ጀቶች ከኢትዮጵያ የአየር ክልል ካፀዳ በኋላ የሶማሊያ ግዛት ዘልቆ በመግባት የነዳጅ ዲፖዎችን ፣ የስንቅና ትጥቅ መጋዘኖችን ፣ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳዎችን ማውደም ተያያዘው ።
  አከታትሎም በሰፊው አውደ ግንባር የተጠመዱትን እሳት የሚተፋትን የጠላትን ስታሊን ኦርጋኖችን ላንቃቸው ዘጋቸው ። የእደላ መስመሮችን ቆረጣቸው።
  የአየር ኃይሉ ጀግኖች አብራሪዎቹ ያለምንም እረፍት በመብረር በአጠቃላይ የወራሪውን ኃይል አናት አናትን እየቀጠቀጡ አዳከሙት ።
የአየር ኃይሉን ሽፋን እየተጠቀመም ህዝባዊ ሰራዊቱ ከህዳር አጋማሽ 1970 ዓ.ም ጀምሮ ከመከላከል ደረጃ ወደ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተሸጋገረ ።
   መሪር መስዋእትነት እየከፈለ የሶማሊያን እግረኛና ሜካናይዝድ ጦርን አከርካሪ መስበሩን ቀጠለበት ። በጠላት ከበባ ወድቀው የነበሩት ድሬዳዋን እና ሀረር ከተሞችን ከጠላት መንጋጋ አስጥሎ ለቀጣዩ ወሳኝ ፍልሚያ ተዘጋጀ
የካቲት 23 /1970 ዓ.ም የዓድዋ ድል እለት የትዮጵያ ጦር  በጭናቅሰን እና በቆሬ በኩል ወደ ጅጅጋ አቅጣጫ የተጠናከረ ቅንጅታዊ የጎህ መጥቃት ዘመቻ ከፈተ ። የሶማሊያ ጦርም ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ብሎ ካልጠበቀው አቅጣጫ በመወጋቱ ተደናገጠ ። ጅጅጋንም ላለመልቀቅ ተሟሟተ ። ሶማሊያ በዚህ መደናገጥ ውስጥ እያለች ከጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ተከፈተባት ። የሶማሊያም ሰራዊት ጅጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል ። በመሆኑም ከጅጅጋ በስተምእራብ በኩል ባለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን በመስራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላከለ ። ሆኖም በለስ አልቀናውም ።
ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመሆኑ አጋዥ ሰራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም ። በውጤቱም የካቲት 26 ረፋድ ላይ በካራማራ ከባድ ሽንፈት ተጎነጨ ። በውጤቱም ከሞትና መቁሰል የተረፈው የጠላት ሠራዊት መሳሪያውን እያንጠባጠበ ጅጅጋን በመልቀቅ ወደ ሀርጌሳ መስመር ፈረጠጠ ።
እሁድ የካቲት 26/1970 ዓ/ም ላይ በአከባቢው የነበረ ሰራዊት ወድቃና ተዋርዳ የነበረችውን  ሰንደቃችንን መልሶ ከፍ አድርጎ በክብር ሰቀለ ። የዛሬ 42 አመት እንዳይድን እንዳይሽር ተደርጎ የተሰበረው የዚያድባሬ ተስፋፊ ኃይል በቀጣይ ቀናቶች ጦርነቱን በይፋ አቁሞ በወረራ ተቆጣጥሯቸው ከነበረው ከቀሪ የኢትዮጵያ ሉኣላዊ መሬቶች ተጠቃሎ ወጣ ። ይህ ድል እውን እንዲሆን ግን የበርካታ ውድ ኢትዮጵያዊያን የደምና የአጥንት መስዋእትነት አስፈልጎ ነበር ። ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪም የወንድም ህዝብ ልጆች የሆኑት የኩባዊያንና የደቡብ የመናዊያን ውድ የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበታል ።
የደረሰው ጉዳት በአጭሩ ይህን ይመስላል ።
ሠራዊት       የሞተ           የቆሠለ          የተማረከ
ኢትዮጵያ         18,000        29,000         450
ኩባ                  163                                   1
የመን                100
ሶማሊያ         15,900       26,200         1,785
  የካራማራ ድል ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሉአላዊነት ያላቸውን ቀናኢነት ቀፎ እንደተነካ ንብ በህብረት በመቆም ገልፀውታል ። ለሠንደቃቸው ያላቸውን ልባዊ ፍቅር ውድ መስዋዕትነት በመክፈል በደማቅ የደም ቀለም ፅፈውታል ። ለዘመናት የተገመደው የማይበጠስ አንድነታቸውን በደም ፍሳሻቸውና በአጥንት ፍላጫቸው በድጋሚ በፅኑ መሠረት ላይ ገንብተውበታል ።
   ከታላቁ የዓድዋ ድል ቀጥሎ የኢትዮጵያዊያን ህብረትና አንድነት ማሳያ የሆነው የካራማራ ጦርነት ለማመን የሚቸግሩ በጀብድ የተሞሉ ጀግንነቶች በተናጠልና በቡድን ተከናውነውበታል። ተዘርዝረው ከማያልቁ የሠራዊቱ ጀብዶች መካከል ለምሳሌ ያህል ሁለቱን ልጥቀስ ።
  የሀረር አካዳሚና የበረራ ት/ቤት ጥምር ምሩቅ የሆኑት የአዲስ አበባው ፍሬ  የአየር ኃይሉ ነብር ጀግናው ብ/ጀ ለገሰ ተፈራ በF5-E ጀታቸው አማካይነት በአየር ላየር ላይ ውጊያ አምስት የሶማሊያ ሚግ 21 ጀቶችን በመምታት ከአየር ወደ መሬት አራግፏቸዋል።
  በርካታ ጀብድ ፈጽመው የድሉ መጨረሻ ሰአት ላይ በፊልቱ ግንባር ላይ አውሮፕላናቸው ተመትቶ በጠላት ተይዘው ለ11 አመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች የስቃይ ህይወት አሳልፈው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
  ለወደር የለሽ የጀግንነት ስራቸውም በጊዜው የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ የሆነውን የህብረተሠባዊት ኢትዮጵያ ወደር የለሽ የጀግና ሜዳይ ተሸልመዋል ።
  ሌላው ጀግና ደግሞ የእናት ሀገር ጥሪ ሰምቶ በለጋ እድሜው ከቀድሞ ወለጋ ክ/ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ የመጣው ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ነው።
  ጀግናው አሊ በአቡሸሪፍ ግንባር  ሶስት የጠላት ታንኮችን በእጅ ቦንብ በማቃጠል በግንባሩ ለነበረው ድል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ። ለዚህም ስራው የላቀ የጀብድ ሜዳይ ተሸላሚ ሆኗል ።
  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት የብሔርና የሀይማኖት አጥር ሳያግዱት በጠነከረ የአንድነት መንፈስ በመላበስ ደሙን አፍስሶ ፣ አጥንቱን ከስክሶ ነው ይህንን ታላቅ ድል ማስመዝገብ የተቻለው።
   ይህ ድል ዕውን እንዲሆን ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪም የወንድም ህዝብ ልጆች የሆኑት የኩባዊያን የሩሲያውያንና የደቡብ የመን ውድ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበታል።
   ዘንድሮ 42 ዓመት የሚሞላውን የካራማራ ድል የመታሠቢያ በዓል ነገ ሐሙስ የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት የመታሠቢያ ፓርክ (ትግላችን ሐውልት) ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ ሀገር ወዳድ እና ታሪክን ዘካሪ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዕለቱ በቦታው በመገኘት የድሉን በዓል ላይ እንድትታደሙ ከወዲሁ እንጋብዛለን።
   መንግስት በቀጣይ ይህንን ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መንፈስ በህይወትና በአካል መስዋዕትነት የከፈሉበትን ታላቅ ሀገራዊ የህዝብ ድል ትኩረት ሰጥቶት በቀጣይ ጊዜያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲከበር እና ትውልዱ አባቶቹ ከሰሩት ከዚህ የጋራ የድል ታሪክ ተምሮ አንድነቱን እንዲያጠነክር አበክሮ እንዲሰራ ጥሪ እናስተላልፋለን።
ተፈፀመ!!!!
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖቹ የካራማራ ሠማእታት ይሁን  !!!
ኢትዮጵያ ምንግዜም በክብር ትኑር !!!
Filed in: Amharic