Followers

Sunday, October 15, 2017

ቢሾፍቱ ለጣና የጻፈው ደብዳቤ!!! በመንግስቱ ዘገየ




ቢሾፍቱ ለጣና የጻፈው ደብዳቤ! !!!
አካም አካም ጣና
ያማሮቹ ማተብ የአባይ ባልንጀራ
በውሃህ ገመገም  
ጨለማ ምትገልጥ ህልም የምታጠራ
የጎጃም ማርሸት ያባይ ዳር ወለላ
አፌ ይጣፍጣል
ወንድም አለም ብዬ ስምህን ስጠራ
ያልሰማሁ መስየ፤
እኔስ ሰምቻለሁ  
ከሚመላለሰው ከሳር ከቅጠሉ
የክፉ ቀን ጓዴ
ህመሜን ነግረውት
መጥቶ ሳይጠይቀኝ ትለኛለህ አሉ
መቼስ ወንድም አለም
ሁሉም በሽተኛ  
ሁሉም ህመምተኛ  
በሆነበት ጓዳ ትንፋሽ ይናፍቃል
እግዚሃር ይማርህ  
የሚለው የሰው ቃል አድራሻው ይርቃል
ግን እንዲህም ሆኖ
አዎን ወንድም አለም
ጦቢያ ከምትባል  
ከኩሾች ምንጭ ስር የፈለቀ ውሃ
በሴረኞች መሃል
ጋንጩር እየዳሰ
ሲጠብል ይኖራል የፍቅር አምሃ
እናም የናቴ ልጅ
መልክህና መልኬ
የተሳለበትን
ያንን ንጹህ ውሃ
በእበትና አዛባ እያደፈረሱ
የወንዙን ዳር ዋርካ
ምስክር እንዳይሆን
በክፋት መጥረቢያ እየገነደሱ
አጥርተህ እንዳታየኝ
አጥርቼ እንዳላይህ  
በድፍርስ ውሃ ላይ ጭቃ እየከለሱ
ስምህን ያጠፉት
እነዚያ ጉንዳኖች ወደየት ደረሱ? ??
ዛሬማ ቀን ወጥቶ
በድፍርሱ መሃል
የጦቢያን ውብ አይኖች
አሻግረው የሚያዬ ፍኖዎች ተነሱ
ጣናም እስካንኬኛ
አባይ እስካንኬኛ
ሰማዩም አፈሩም ገረቢያ ኬኛ
በሚል ውብ ዝማሬ እየተጫፈሩ
የሰላሌ ልጆች
ዳዋና ቆንጥሩን እየመነጠሩ
ጣና ከሃይቁ ዳር
ስለ ፍቅር ብለው ሺህ ፍቅር ገበሩ
አየህልኝ ጣና
አሞታል ብለውኝ
ሰምቼማ ነበር ከሁሉ አስቀድሜ
ሳልመጣ የቀረሁ
ግራ ቢገባኝ ነው ፤ጠንቶብኝ ህመሜ
ይኸው ወንድም አለም
ሆራ መልከ ሰዲ
አበባ ረግፎብኝ ከሃይቁ ገመገም
እናላቅስሽ ብሎ
ያልተንሰቀሰቀ ያላዘነ የለም
ካዘኔ ስነሳ
እመጣለሁ ብዬ ወጥቼ ከቤቴ
ይኸውልህ ዛሬ
የልጄን ሙት አመት
ካወጣሁ በሃላ
ጣና ወንድሜ ጋር
ልላቀስ መጣሁኝ
እንደ ደጉ ዘመን እንደልጅነቴ
እናም ወንድም አለም
ከውሃችን ገላ
አይን የሚገደግድ አፈር እየረጩ
አጥርተን እንዳናይ
ያይናችንን ጭራ
ዘግነው የጨረሱ በሜንጦ እየነጩ
ብካይ ትንቢታቸው
የጦስ ንግርታቸው  
በጦቢያ መዶሻ ስለተወቀጠ
ያመገሉት ቁጭት
በፍቅር ወረንጦ ሙጀሌው ፈረጠ
ዛሬማ ዛሬማ
እንደ ንስር ብሌን
ካድማስ ባሻጋሪ  
ጨለማና ግፉን እየመነጠረ
ሸርና ጭንገፋን
ለይቶ የሚገፍ
ባይኖቹ ብርሃን እየበረበረ፤
ይኸው በኛ ቀዬ
ኢጆሌ ኦሮሞ
ቢያን ኬኛ ብሎ ጣና ዳር አደረ
ዛሬ በድፍርሱ
በውሀው መልክ ላይ  
በዳበሳ ፍቅር ፊደል ለይተናል፤
የማይታየውን
የብርሃን ቀለም
በጨለማ መሃል ማየት ጀምረናል
ይህንን ብርሃን
ከእጃችን ለማስጣል፤ 
በደረቀ መንፈስ ለሚንገዳገዱ
በዲማው ጊወርጊስ
ከጋንጩር ጋር ሲኦል መቀመቅ ይውረዱ
አሜን! !!!  

No comments:

Post a Comment