Followers

Sunday, October 15, 2017

ቢሾፍቱ ለጣና የጻፈው ደብዳቤ!!! በመንግስቱ ዘገየ




ቢሾፍቱ ለጣና የጻፈው ደብዳቤ! !!!
አካም አካም ጣና
ያማሮቹ ማተብ የአባይ ባልንጀራ
በውሃህ ገመገም  
ጨለማ ምትገልጥ ህልም የምታጠራ
የጎጃም ማርሸት ያባይ ዳር ወለላ
አፌ ይጣፍጣል
ወንድም አለም ብዬ ስምህን ስጠራ
ያልሰማሁ መስየ፤
እኔስ ሰምቻለሁ  
ከሚመላለሰው ከሳር ከቅጠሉ
የክፉ ቀን ጓዴ
ህመሜን ነግረውት
መጥቶ ሳይጠይቀኝ ትለኛለህ አሉ
መቼስ ወንድም አለም
ሁሉም በሽተኛ  
ሁሉም ህመምተኛ  
በሆነበት ጓዳ ትንፋሽ ይናፍቃል
እግዚሃር ይማርህ  
የሚለው የሰው ቃል አድራሻው ይርቃል
ግን እንዲህም ሆኖ
አዎን ወንድም አለም
ጦቢያ ከምትባል  
ከኩሾች ምንጭ ስር የፈለቀ ውሃ
በሴረኞች መሃል
ጋንጩር እየዳሰ
ሲጠብል ይኖራል የፍቅር አምሃ
እናም የናቴ ልጅ
መልክህና መልኬ
የተሳለበትን
ያንን ንጹህ ውሃ
በእበትና አዛባ እያደፈረሱ
የወንዙን ዳር ዋርካ
ምስክር እንዳይሆን
በክፋት መጥረቢያ እየገነደሱ
አጥርተህ እንዳታየኝ
አጥርቼ እንዳላይህ  
በድፍርስ ውሃ ላይ ጭቃ እየከለሱ
ስምህን ያጠፉት
እነዚያ ጉንዳኖች ወደየት ደረሱ? ??
ዛሬማ ቀን ወጥቶ
በድፍርሱ መሃል
የጦቢያን ውብ አይኖች
አሻግረው የሚያዬ ፍኖዎች ተነሱ
ጣናም እስካንኬኛ
አባይ እስካንኬኛ
ሰማዩም አፈሩም ገረቢያ ኬኛ
በሚል ውብ ዝማሬ እየተጫፈሩ
የሰላሌ ልጆች
ዳዋና ቆንጥሩን እየመነጠሩ
ጣና ከሃይቁ ዳር
ስለ ፍቅር ብለው ሺህ ፍቅር ገበሩ
አየህልኝ ጣና
አሞታል ብለውኝ
ሰምቼማ ነበር ከሁሉ አስቀድሜ
ሳልመጣ የቀረሁ
ግራ ቢገባኝ ነው ፤ጠንቶብኝ ህመሜ
ይኸው ወንድም አለም
ሆራ መልከ ሰዲ
አበባ ረግፎብኝ ከሃይቁ ገመገም
እናላቅስሽ ብሎ
ያልተንሰቀሰቀ ያላዘነ የለም
ካዘኔ ስነሳ
እመጣለሁ ብዬ ወጥቼ ከቤቴ
ይኸውልህ ዛሬ
የልጄን ሙት አመት
ካወጣሁ በሃላ
ጣና ወንድሜ ጋር
ልላቀስ መጣሁኝ
እንደ ደጉ ዘመን እንደልጅነቴ
እናም ወንድም አለም
ከውሃችን ገላ
አይን የሚገደግድ አፈር እየረጩ
አጥርተን እንዳናይ
ያይናችንን ጭራ
ዘግነው የጨረሱ በሜንጦ እየነጩ
ብካይ ትንቢታቸው
የጦስ ንግርታቸው  
በጦቢያ መዶሻ ስለተወቀጠ
ያመገሉት ቁጭት
በፍቅር ወረንጦ ሙጀሌው ፈረጠ
ዛሬማ ዛሬማ
እንደ ንስር ብሌን
ካድማስ ባሻጋሪ  
ጨለማና ግፉን እየመነጠረ
ሸርና ጭንገፋን
ለይቶ የሚገፍ
ባይኖቹ ብርሃን እየበረበረ፤
ይኸው በኛ ቀዬ
ኢጆሌ ኦሮሞ
ቢያን ኬኛ ብሎ ጣና ዳር አደረ
ዛሬ በድፍርሱ
በውሀው መልክ ላይ  
በዳበሳ ፍቅር ፊደል ለይተናል፤
የማይታየውን
የብርሃን ቀለም
በጨለማ መሃል ማየት ጀምረናል
ይህንን ብርሃን
ከእጃችን ለማስጣል፤ 
በደረቀ መንፈስ ለሚንገዳገዱ
በዲማው ጊወርጊስ
ከጋንጩር ጋር ሲኦል መቀመቅ ይውረዱ
አሜን! !!!  

Friday, October 6, 2017

የኢትዮጵያዊነት ችግር ኢትዮጵያ አይደለችም (መስፍን ወ/ማሪያም)


"የኢትዮጵያዊነት ችግር ኢትዮጵያ አይደለችም፣ችግሩ የሥርዓት ችግር ነው። የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ እንዳለው ቂል እንዳንሆን።" ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም (የኔታ)
_______________________________//______________________________
ኢትዮጵያዊነት ብዙ የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተዋኅዱበት አካል ክፍል መሆን ነው። ኢትዮጵያዊነት ከጎሠኝኛት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የዚች ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት፣ የደጋው ዝናም ከቆላው ወንዝ ጋር የተዛመደበት ኃይል ነው።ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ ለክርስቶስና ለመሐመድ የሚጨሰው ዕጣን በእርገት መጥቶ የሚደባለቅበት እምነት ነው።ኢትዮጵያዊነት በቄጤማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው።
ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣የሚዛናዊነት የጨዋነት ባሕርይ ነው።ኢትዮጵያዊነት ረዢምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰዉለት ስሜት ነው።ኢትዮጵያዊነት ስቃይና መከራ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብርም ነው።ኢትዮጵያዊነት ጭቆናና ጥቃት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሻፈረኝና እምቢ ባይነትም ነው።የኢትዮጵያዊነት ዓላማ ያለችውንና የኖረችውን ኢትዮጵያን እንደገና ለመፍጠር አይደለም።
የኢትዮጵያ ዓላማ ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚስማማ እድገታቸውንም የሚያፋጥንና፣ኅብረታቸውን የሚያጠነክር ሥርዓትን መፍጠር ነው። የኢትዮጵያዊነት ችግር ኢትዮጵያ አይደለችም፣ችግሩ የሥርዓት ችግር ነው። የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ እንዳለው ቂል እንዳንሆን።ኢትዮጵያዊነትን መካድ የራስን ማንነት መካድ ብቻ አይደለም። አባቶችንና እናቶችን፣ቅድም አያቶችን ከነቅርሳቸው መካድ ነው።
በእንደዚህ ዓይነቱ ክህደት ላይ የተመሰረተ ማንነት የት ይደርሳል?ከበሽታ በቀርስ ትርፉ ምን ይሆናል? ክህደት ራሱን የቻለ በሽታ ሲሆን ማስካድ ደግሞ የባሰ ነው። ክዶ ማስካድ ታምሜያለሁኝ፣ ታመሙ እንደማለት ነው። አስታማሚ እንኳን እንዳይገኝ የማድረጉ ጥረት የበሽታውን ምለዓትና ጽናት ያመለክታል።ሆኖም የኢትዮጵያ ታሪክ ሊያስተምረን እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት እንደ ላስቲክ ነው። ሲስቡት ይሳባል፣ሲለቁት ይሰበሰባል። ማለት-ይሳብና ይሳሳል እንጂ አይበጠስም።
ምንጭ ኢትዮጵያ ከየት፣ወዴት? ገጽ 31-32 መስፍን /ማሪያም1986 ..


Wednesday, October 4, 2017

ብሄር ከብሄረሰብ ይለያል ?ከተለየስ እንዴት? አብራሃም ለቤዛ



ብሄር ማለት አገር ማለት ነው፤ ብሄረሰብ ደግሞ የአገር አባላት ፡፡ ልክ ቤት ብለን ቤተሰብ እንደማለት፡፡ ታዲያ ይኸ በኢትዮጵኛ እንጂ በአልባኒያኛ አይደለም፡፡ የአልባንያው ደብተራ በዚህ አይስማማም፡፡
ብሄራዊ ቡድን፤ ብሄራዊ ባንክ፤ ብሄራዊ ሎተሪ፤ ብሄራዊ ትያትር፤ ብሄራዊ ሊግ፤ ብሄራዊ በዓል፤ ብሄራዊ የሃዘን ቀን፤ ብሄራዊ መዝሙር፤ብሄራዊ ጂን ሳይቀር ኢትዮጵያዊያንን ማዕከል አድርገው የተቋቋሙ ተቋሞቻችን እና እሴቶቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋሞቻችን እና እሴቶቻችን  ታዲያ አንድ አካል አንድ አምሳል ሁነው ነው የኢትዮጵያችን (የአገራችን) ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ ከአንድ በላይ ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ብሄር ከፍ ያለ የዳበረ ማንነት ያለው ፤ ብሄረሰብ ደግሞ አነስ ያለ ወደ ብሄር ደረጃ በመንደርደር ላይ ያለ ማንነት የሚለው አልባኒያዊ ትርጎሜ ፉርሽ ነው፡፡  
ከዛሬ 22 ዓመት ወዲህ በኢትዮጵዊያን መታወቂያ ብሄር የሚል ጥያቄ ይቀርባል ፡፡ በርግጥ በ19 87 ዓ/ም በወጣው ህገ-መንግስት ኢትዮጵያ የብሄር ፣ብሄረሰቦች ህዝቦች ሉዓላዊ ግዛት ነች ይላል፡፡ በጣም አደገኛ የሆነው የህገ-መንግስቱ ግልባጭ ወደ ክልሎች ሲወርድ ክልላችን የእንቶ ፈንቶ ፤ ቡራ ከረዩ  እና ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ብሄረሰቦች ሉዓላዊ ግዛት ብቻ ነው ሲል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አሁኑኑ አትሉም፡፡ የጎሳ ማንነታችንን ኢትዮጵያ (ብሄር-አገር) በሚለው እየተካን በቋንቋ ላይ ደባ እየፈጸምን እንገኛለን፡፡ ብሄር አገር ነው ካልን ዘንዳ ዜግነት ከሚለው ጋር ይስተካከልል፡፡  
United Nations የሚለው የተባበሩት አገሮች የሚል አቻ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ቢያንስ ዓለም ሉዓላዊነታቸውን ያወቀላቸው አገሮች ትብብር ነው፡፡ ወደ እኛ ሰንመጣ ይኸው በአልባንያኛ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የብዙ ብሄሮች ስምምነት (ትብብር) ውጤት ዕንጂ አንድ አገር አይደለችም ነው፡፡ አንድ አገር ፤አንድ ህዝብ ፤ አንድ ሰንደቅ ዓላማ አትሉም፡፡
ይኸን ሃሳብ የቋንቋ ባለሙያዎች የበለጠ ልታዳብሩት ትችላለችሁ፡፡ ለውይይት ክፍት ነው፡፡